ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የትዊተር ሥራ አስፈጻሚ ጃክ ዶርሲ ከኃላፊነቱ ሊለቅ መሆኑ ተነገረ
የትዊተር አንዱ መስራች ጃክ ዶርሲ ከኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚነት ኃላፊነቱ ሊለቅ መሆኑን የተለያዩ ዘገባዎች አመለከቱ።
ዶርሲ ታዋቂ ከሆኑትና በርካታ ተጠቃሚ ካላቸው የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች አንዱ የሆነውን ትዊተርን ከ15 ዓመት በፊት የመሠረተ ሲሆን፣ የክፍያ አገልግሎት ተቋም የሆነውን 'ስኩዌር' እና የትዊተር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል።
ባለፈው የፈረንጆች ዓመት አንዳንድ ወገኖች ትኩረቱን በአንድ ተቋም ላይ ብቻ እንዲያደርግ በመጠየቅ ከኃላፊነቱ እንዲለቅ ግፊት ሲያደርጉበት ነበር።
የጃክ ዶርሲ ከኃላፊነቱ ሊለቅ መሆኑ ወሬ ከተሰማ በኋላ የትዊተር የአክሲዮን ድርሻ ዋጋ በተወሰነ መጠን ጨምሯል።
የዶርሲ ኃላፊነት መልቀቅ መጀመሪያ የተዘገበው ዛሬ ሰኞ ሲሆን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ናቸው ዜናውን ይፋ ያደረጉት። ሮይተርስ የዜና ወኪልም በተመሳሳይ ዜናውን ዘግቦታል።
የ45 ዓመቱ ዶርሲ ትዊተርን ከቢዝ ስቶን፣ ኢቫን ዊሊያምስ እና ከኖህ ግላስ ጋር በመሆን ነበር ያቋቋመው።
ቢሆንም ግን የመጀመሪያዎቹን የትዊተር መልዕክቶችን በማስተላለፍና ለረጅም ዓመታት በዋና ሥራ አስፈጻሚነት በማገልገል ከኩባንያው ስም ጋር በቀዳሚነት የሚነሳው ጃክ ዶርሲ ነው።
ዶርሲ እንደ አውሮፓውያኑ 2008 ትዊተርን በመልቀቅ የዲጂታል ክፍያ መተግበሪያ የሆነውና ባለብዙ ቢሊዮን ዶላር ኩባንያ የሆነውን 'ስኩዌር'ን መስርቶ እየሰራ ነበር።
ነገር ግን ከሰባት ዓመት በኋላ የትዊተር ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበረው ዲክ ኮስቶሎ ሥራውን መልቀቁን ተከትሎ ወደ ትዊተር ተመልሷል።
ዶርሲ ኃላፊነቱን እንዲለቅና ትዊተር ሙሉ ጊዜውን በኩባንያው ሥራ ላይ ብቻ ያተኮረ ሥራ አስፈጻሚ እንዲኖረው ግፊት ሲደረግ ቆይቷል።
በትዊተር አመራር ላይ ከሚደረገው ለውጥ በተጨማሪ በኩባንያው ቦርድ ዙሪያ በርካታ ለውጦች የተደረጉ ሲሆን፣ የተለያዩ አዳዲስ ሹመቶችም እየታዩ ነው።