ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሕንድ ፍርድ ቤት በህጻናት ጥቃት ዙሪያ የሚሰጠውን ቅጣት መቀነሱ ቁጣን ቀሰቀሰ
የሕንድ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በ12 ዓመቷ ልጅ ላይ ፆታዊ ጥቃት ፈጽሟል የተባለው ግለሰብ ከተጠቂዋ ጋር "የቆዳ ለቆዳ ንክኪ አልፈጠረም" በሚል አወዛጋቢ ውሳኔ በመስጠቱ እና በሌላ የፍርድ ውሳኔ የ10 ዓመት ወንድ ልጅ ላይ የአፍ ወሲባዊ ጥቃት የፈጸመን ግለሰብ የእስር ጊዜ እንዲቀንስ ማድረጉ ቁጣ ቀስቅሷል።
የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ይፋ የተደረገው በሰሜን ኡታር ፕራዴሽ ግዛት የሚገኘው አላባድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው።
በሕጻኑ ላይ የወሲባዊ ጥቃት ወንጀሉ የተፈፀመው ከአራት ዓመት በፊት ሲሆን ልጁ ስለ ድርጊቱ እንዳይናገር 10 ብር ገደማ ከመስጠት ባለፈ ስለጉዳዩ ቢያወራ ከባድ መዘዝ እንደሚያስከትል አስፈራርቶታል።
ይህንን ክስ የተመለከተው ፍርድ ቤት ግለሰቡን "በከባድ የወሲብ ጥቃት" ጥፋተኛ ብሎ የ10 ዓመት እስራት ፈርዶበት ነበር።
ሰውዬው ይግባኝ በመጠየቁ ባለፈው ሳምንት ጉዳዩን ያየው የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ በሕጉ መሰሠረት ጥቃቱ "ኃይል ተቀላቀለበት አይደለም" በማለት የእስር ጊዜውን ወደ ሰባት ዓመት ዝቅ አደረጉት።
የሕግ ባለሙያዎች በሕጉ ውስጥ ጥቃትን "ኃይል የተቀላቀለበት" የሚያደርጉ በርካታ ምክንያቶች እንዳሉ በመግለጽ ውሳኔውን ኮንነዋል።
ውሳኔውን በርካቶች ወደ በማኅበራዊ ሚዲያ በማምጣት እንዲተቹ ከማድረግ ባለፈ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሙምባይን ከፍተኛ ፍርድ ቤት "የቆዳ ለቆዳ ንክኪ የለም" የሚለውን ወደ ጎን በመተው የድርጊቱን ዝርዝር ጉዳዮች ሳይሆን "የወሲብ ፍላጎትን" ማጤን አለበት ያለው ባለፈው ሳምንት እንደነበር ብዙዎች ጠቁመዋል።
አንድ የትዊተር ተጠቃሚ ውሳኔውን "አሳዛኝ እና እንግዳ" ሲል ገልጿል።
ሌላው ደግሞ "ምንም ዓይነት ቅጣት የዚያን ትንሽ ልጅ ጉዳት ሊጠግነው አይችልም" ሲል ጽፏል። ብዙዎች ደግሞ "ዳኛው ምን ነክቶታል?" ብለዋል።
የአገሪቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ማሁ ሞይተራ ውሳኔው ላይ ቁጣቸውን በትዊተር ከገለጹት መካከል ይጠቀሳሉ።
"ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ንቁ። ሕጉ ልጆችን ከከባድ ወንጀሎች ለመታደግ የተሰራ ነው" ሲሉም ጽፈዋል።
ሕንድ በዓለማችን ከፍተኛ የህጻናት ፆታዊ ጥቃት የሚመዘገብባት ሲሆን በየዓመቱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ክስተቶች ሪፖርት ይደረጋሉ።
ባለፈው ዓመት የብሔራዊ የወንጀል መዛግብት ቢሮ 43,000 ወንጀሎችን መዝግቧል። ይህም በየ12 ደቂቃው በአማካይ አንድ ወንጀል ይፈጸማል ማለት ነው።
ፖሊስ በበኩሉ ልክ እንደ 10 ዓመቱ ልጅ ከ90 በመቶ በላይ የሆኑትን ወንጀሎች የሚፈጽሙት በተጠቂዎቹ ይታወቃሉ።
ለሩብ ምዕተ ዓመት በልጆች ላይ የሚፈጸመውን ጾታዊ ጥቃት በተለይም በዘመዶቻቸው የሚደርስ ጥቃትን በተመለከተ ሲሠሩ የቆዩት አኑጃ ጉፕታ፣ አብዛኞቹ ጉዳዮች ሪፖርት ስለማይደረጉ ኦፊሴላዊዎቹ ቁጥሮች ሙሉውን ታሪክ አይናገሩም ብሏል።
"የህፃናት ወሲባዊ ጥቃት የማይነገርለት ወረርሽኝ ተብሎ ይጠራል። በሁሉም ቦታ ይገኛል። በእያንዳንዱ ቤት እና ትውልዶች ውስጥ እየተፈጠረ ነው። ብዙ ጥቃት አድራሾች የቅርብ የቤተሰብ አባላት ስለሆኑ ስለ ጉዳዩ ለመነጋገር ካለው እምቢተኝነት በተጨማሪ መገለልም አለ። ጥቃት የደረሰባቸውን ጨምሮ በቤተሰብ ውስጥ እንፈታዋለን ይላሉ። ስለዚህ ከእያንዳንዱ ፍርድ ቤት ከሚደርሰው ጉዳይ ጎን ለጎን በመቶዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ለሕግ አካል አይደርሱም" ብልዋል።
በህጻንነታቸው ወሲባዊ ጥቃት ደርሶባቸው የነበሩት ራሳቸው ጉፕታ ችግሩ በህይወት እያሉ ስለመቀረፉ እንደማያስቡ ተናግረዋል።
"በእኔ ላይ የደረሰው ነገር በ18 እና በ19 ዓመት ታዳጊዎች ላይ እንደደረሰ አይቻለሁ" ይላሉ።
ሕግ እና የወንጀል ፍትህ ሥርዓቱ አንድ ጣልቃ ገብነት ብቻ ሲሆን ትልቁ ጉዳይ ማኅበራዊው ችግር በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።
"ወረርሽኝ ተብሎ ስለሚገለጽ እንደማንኛውም ወረርሽኝ ልንዋጋው ይገባል። መንግሥት፣ ኅብረተሰቡ እና ቤተሰብን ጨምሮ ሁሉም በትግሉ መሳተፍ አለበት። መንግሥት መረጃ መስጠት፣ የፈጠራ ታሪኮችን ማጥፋት፣ ጭፍን ጥላቻ ማስወገድና መፍትሄ መስጠት አለበት።"
የመጀመሪያው እርምጃ ግን ችግሩ ስለመኖሩ ማመን እና ስፋቱንም መቀበል ነው ሲሉ ጉፕታ ያምናሉ። "አለማመን በኅብረተሰባችን ውስጥ ተስፋፍቷል:: በግልም ሆነ በቡድን እንክዳለን:: በጉዳዩ ላይ መነጋገር አለብን። ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ፍላጎት ለምናደረገው ሁሉ ማዕከል መሆን አለበት" ብለዋል።