ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ድምጻዊ አር ኬሊ ለወሲባዊ ብዝበዛ ሴቶችና ሕጻናትን በማዘዋወር ጥፋተኛ ተባለ
አሜሪካዊው ድምጻዊ አር ኬሊ ላለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት ዝናውን በመጠቀም በሴቶችና ህጻናት ላይ ወሲባዊ ጥቃት በመፈፀም እና በማቀነባበር ጥፋተኛ ተባለ።
ዘጠኝ ሴቶችና ሁለት ወንዶች በአጠቃላይ አስራ አንዱ ከሳሾች በድምጻዊው ተፈፀመ ያሉትን ወሲባዊ ትንኮሳ እና ጥቃት ምስክርነታቸውን ለመስጠት ከባድ የሆነውን የ6 ሳምንታት የፍርድ ሂደት ተከታትለው ነበር።
ዳኞች ውሳኔ ላይ ለመድረስ ጉዳዩን ለሁለት ቀናት ከመረመሩ በኋላ ኬሊ በቀረቡበት ሁሉም ክሶች ጥፋተኛ ሆኖ አግኝተውታል።
የመጨረሻ ብይን ለመስጠትም ለግንቦት አራት ቀን የተቀጠረ ሲሆን ድምጻዊው ቀሪ ዘመኑን ዘብጥያ ሊያሳልፍ ይችላል ተብሏል።
በሙሉ ስሙ ሮበርት ስይልቨስተር ኬሊ በመባል የሚታወቀው ድምጻዊ አር ኬሊ በሴቶችና ህጻናት ላይ ወሲባዊ ጥቃት እንዲፈፀም የማታለል እና የማስገደድ እቅድ መሪ ነበርም ብለዋል ዳኞቹ።
ሽልማት ባገኘበትና 'አይ ቢሊቭ አይ ካን ፍላይ' በሚለው የሙዚቃ ሥራው የሚታወቀው ድምጻዊው ከተለያዩ የአሜሪካ ክፍለ አገራት ሴቶችን በሕገ ወጥ መንገድ በማዘዋወር እና የሕጻናት የወሲብ ፊልም በማዘጋጀት ጥፋተኛ ተብሏል።
አር ኬሊ ከቀረቡበት ስምንት ለወሲባዊ ብዝበዛ የሴቶች ሕገ ወጥ ዝውውር ክሶች በተጨማሪ በማጭበርበር ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቷል። ይህ ክስ በአብዛኛው በተደራጁ የወንጀል ማሕበራት ላይ የሚቀርብ ነውም ተብሏል።
በፍርድ ሒደቱ አቃቤ ሕግ የአር ኬሊ ሥራ አስኪያጆች፣ ጠባቂዎች እና ሌሎች አባላት በወንጀል ሥራው ውስጥ እሱን ለመርዳት እንዴት እንደሠሩ በዝርዝር አስረድተዋል።
አንዲት ሴት አር ኬሊ እንዳሰራት፣ በእፅ እንዳደነዘዛትና እንደደፈራት ከፍርድ ውሳኔው በኋላ በጽሁፍ በሰጠችው ምስክርነት ገልጻለች።
ሴትዮዋ ክሷን በአደባባይ ከተናገረች በኋላ "ማስፈራሪያና ዛቻዎች ይደርሱብኝ ነበር" በማለት ከአር ኬሊ ተደብቃ ነበር ቃሏን የሰጠችው።
" አሁን ሕይወቴን ከስጋት ነጻ ሆኘ ለመጀመርና ለማገገም ዝግጁ ነኝ" ስትልም በፍርድ ቤቱ ሶንጃ ተብላ የተገለፀችው ይህች ሴት ተናግራለች።
ሕጋዊ ሰነዶችም አር ኬሊ በተጎጂዎቹ ላይ ያደረሰውን የአዕምሮ ስቃይ ያመላከቱ ሲሆን ያለ እሱ ፈቃድ ምግብ እንዲበሉ ወይም መጸዳጃ ቤት እንዲሄዱ አይፈቀድላቸውም ነበር።
ከዚህም በተጨማሪ የሚለብሱትን ልብስ የሚቆጣጠር ሲሆን 'ዳዲ' ብለው እንዲጠሩትም ያስገድዳቸው ነበር።
በርካታ የጥቃቱ ሰለባዎችን የወከሉት የሕግ ባለሙያዋ ግሎሪያ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ "ላለፉት 47 ዓመታት በሕግ ሙያ ሰርቻለሁ። በእነዚህ ጊዜያት በርካታ በሴቶችና ሕጻናት ላይ ወሲባዊ ጥቃት ፈጻሚዎችን ጉዳይ ተከታትያለሁ። ከዚህ ሁሉ ግን አር ኬሊ ያደረገው የከፋ ነው" ብለዋል።
ሰኞ እለት ከፍርድ ሒደቱ በኋላ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ አቃቤ ሕግ ጃክሊን ካሱሊስ ዳኛው እንደ አር ኬሊ ላሉ ዝነኞች መልዕክት አስተላልፈዋል ብለዋል።
"ምንም ያህል ጊዜ ይውሰድ ከሕግ ማምለጥ አይቻልም" ብለዋል ካሱሊስ።
ውሳኔው የተላለፈው አር ኬሊ በኢሊኖይ ግዛት ውስጥ በህጻናት የወሲብ ፊልም በማዘጋጀት ክስ ከቀረበበት ከ13 ዓመታት በኋላ ነው።
የተሰሙት አብዛኞቹ ክሶችም በመጀመሪያ እአአ በ2019 'ሰርቪንግ አር ኬሊ' ዘጋቢ ፊልም ውስጥ ተጠቅሰዋል።
የጥቃቱ ሰለባዎች ከሚያዘጋጀው የሙዚቃ ድግስ ታዳሚዎች የተመረጡ ወይም ከድምጻዊው ጋር በአጋጣሚ ከተገናኙ በኋላ ለአዳዲስ የሙዚቃ ሥራዎቻቸው እገዛ ካደረገላቸው በኋላ እርሱን እንዲቀላቀሉ የተታለሉ ናቸው።
ይሁን እንጂ ከተቀላቀሉ በኋላ ጥብቅ ገደቦች የተጣሉባቸው ሲሆን የእርሱ ቡድኖች ' የሮብ ሕጎች' ብለው የሰየሟቸውን ደንቦች ከጣሱ ኃይለኛ ቅጣት ይቀጡ ነበር።