በአውሮፓና አካባቢው እስከ መጋቢት 700 ሺህ ሰዎች በኮቪድ ሊሞቱ ይችላሉ -የዓለም ጤና ድርጅት

ማስክ ያደረገች ሴት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

በአውሮፓ እና በአንዳንድ የእስያ አገራት እስከ መጋቢት ተጨማሪ 700,000 ሰዎች በኮቪድ ሊሞቱ ይችላሉ ሲል የዓለም ጤና ድርጅት አስጠነቀቀ።

የዓለም ጤና ድርጅት የአውሮፓ ክልል ብሎ በሚጠራቸው 53 አገሮች የሟቾች ቁጥር ከ1.5 ሚሊዮን አልፏል።

የዓለም ጤና ድርጅት ከአራት ወራት በኋላ በ49 አገሮች የሚገኙ የጽኑ ህሙማን ክፍሎች "ከፍተኛ ጫና" ሊያጋጥማቸው እንደሚችል አስጠንቅቋል።

ኦስትሪያ ወደ እንቅስቃሴ ገደብ እንድትመለስ እና ሌሎች አገራት አዳዲስ እርምጃዎችን እንዲያስቡ ያስገደደ የአዳዲስ ኮቪድ ታማሚዎች ቁጥር በአውሮፓ እየጨመረ ነው።

ፈረንሳይን፣ ጀርመንና ግሪክን ጨምሮ በርካታ አገራት ሙሉ በሙሉ የተከተቡ ዜጎቻቸው በቅርቡ ተጨማሪ የኮቪድ ክትባት እንዲያገኙ ሊያደርጉ ይችላሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በበርካታ አገራት አዳዲስ እርምጃዎችን በመቃወም ከፍተኛ ተቃውሞዎች ተጀምረዋል። ኔዘርላንድስ ከደነገገችው ከፊል እገዳ ጋር በተያያዘ በርካታ ምሽቶችን በብጥብጥ ውስጥ አሳልፋለች።

የዓለም ጤና ድርጅት ባደረገው ግምገማ አውሮፓ በሚለው ክልሉ ውስጥ ዋነኛው የሞት መንስኤ ኮቪድ-19 ነው ሲል አስጠንቅቋል።

"አሁንባለው አዝማሚያ መሠረት በመጪዎቹው የፀደይ ወራት የሟቾች ቁትር ከ2.2 ሚሊዮን በላይ እንደሚደርስ ተተንብይዋል" ሲል የዓለም ጤና ድርጅት ማክሰኞ አስታውቋል።

ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ የሚከሰተው ሞት በእጥፍ አድጎ 4,200 የሚጠጉ ሰዎች በቀን ጨምረዋል ሲል አክሏል።

በቅርቡ በሩሲያ ብቻ በየዕለቱ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ1,200 በላይ ሆኗል።

በአውሮፓ ክልል ላለው ከፍተኛ ስርጭት በርካታ ቁጥር ያላቸው ያልተከተቡ ሰዎችን እና በአንዳንድ አገራት ዴልታ የተሰኘው የቫይረሱ ዝርያ መስፋፋት ቁልፍ ምክንያቶች መሆናቸውን የዓለም ጤና ድርጅት ገልጿል።

የዓለም ጤና ድርጅት የአውሮፓ ዳይሬክተር ዶ/ር ሃንስ ክሉጅ ያልተከተቡ ሰዎች እንዲከተቡ አሳስበዋል።

"ሁላችንም አላስፈላጊ አደጋዎችን እና የህይወት መጥፋትን በመከላከል በኅብረተሰቡ እና በንግዱ ላይ የሚደርሰውን ተጨማሪ መስተጓጎል የመቀነስ ዕድል እና ኃላፊነት አለብን" ብለዋል።

ከአውሮፓ አገራት በተጨማሪ የዓለም ጤና ድርጅት እስራኤልን ጨምሮ እንደ ታጂኪስታን እና ኡዝቤኪስታን ያሉ የቀድሞ የሶቪየት አገራትን እንደ አውሮፓ ክልል ይመለከታቸዋል።