በኔዘርላንድስ የኮቪድ-19 መከላከያ እርምጃን የተቃወሙ ሰልፈኞች ከፖሊስ ጋር ተጋጩ

ተቃዋሚዎች ድንጋይ እና ርችት ከመወርወር ባለፈ የፖሊስ መኪኖችን አቃጥለዋል

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ተቃዋሚዎች ድንጋይ እና ርችት ከመወርወር ባለፈ የፖሊስ መኪኖችን አቃጥለዋል
ታትሟል

በሮተርዳም የተጣሉ አዳዲስ የኮቪድ-19 መከላከያ እርምጃዎችን ተከትሎ አመጽ በመቀስቀሱ የኔዘርላንድስ ፖሊስ የማስጠንቀቂያ ተኩስ መተኮሱ እና የአድማ መበተኛ ውሃ መጠቀሙ ተገለጸ።

ተቃዋሚዎች ድንጋይ እና ርችት ከመወርወር ባለፈ የፖሊስ መኪኖችን አቃጥለዋል።

መንግሥት ያቀረበውን የኮቪድ-19 ክትባት ዕቅድ እና በአዲስ ዓመት ዋዜማ ርችቶች እንዳይተኮሱ መከልከሉን በመቃወም በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ቁጣቸውን ለማሰማት ተሰብስበው ነበር።

በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ኔዘርላንድስ ባለፈው ሳምንት ለሦስት ሳምንታት የሚቆይ ከፊል የእንቅስቃሴ ገደብ ጥላለች።

የፖሊስ ቃል አቀባይ ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት ፖሊስ የማስጠንቀቂያ ጥይቶችን ፊት ለፊት የተኮሰው "ሁኔታው ለሕይወት አስጊ በመሆኑ ነው" ብለዋል።

በተተኮሰው ጥይት ምክንያት ቢያንስ ሁለት ሰዎች ቆስለዋል ሲሉም አክለዋል።

ሮተርዳም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር የወደቀች ሲሆን በሁከቱ ምክንያት ዋናው የባቡር ጣቢያ ተዘግቷል።

በማኅበራዊ ድር አምባዎች ላይ በተለቀቁ ቪዲዮዎች የተቃጠሉ የፖሊስ መኪኖችና ሰልፈኞቹ በከተማዋ ዋና ዋና የገበያ መንገዶች የታዩ ሲሆን፣ ተቃዋሚዎች ወደ ፖሊስ ድንጋይ ሲወረውሩ ነበር።

ወረርሽኙ ከጀመረበት ጊዜ ወዲህ ኔዘርላንድስ ከፍተኛውን የኮቪድ-19 ተያዦች ቁጥር በማስመዝገቧ ባለፈው ቅዳሜ አዳዲስ ገደቦችን ጥላለች።

በእርምጃዎቹ መሠረት ምግብ ቤቶች እና ሱቆች ቀደም ብለው የሚዘጉ ሲሆን ስፖርታዊ ውድድሮች ያለ ተመልካች ይከናወናሉ።

እርምጃው ከተገለጸ በኋላ ተቃዋሚዎች በሄግ ከፖሊስ ጋር ተጋጭተዋል።

የሮተርዳም ተቃዋሚዎች መንግሥት ለተከተቡ ወይም ከቫይረሱ ላገገሙ ሰዎች የሚሰጠውን "የኮሮናቫይረስ ይለፍ ፈቃድ" ለማስተዋወቅ ማሰቡን ተቃውመዋል።

ፈቃዱ ተግባራዊ ከተደረገ ይለፉን የሚያሳዩ ብቻ ቤት ውስጥ ወደሚደረጉ ዝግጅቶች ወይም ምግብ ቤቶች እና መጠጥ ቤቶች መግባት ይፈቀድላቸዋል።

አርብ ዕለት መንግሥት በተከታታይ ለሁለተኛ ዓመት ለፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ዋዜማ ርችቶችን እንዳይተኮሱ ከልክሏል። እገዳው "በጤና አጠባበቅ ሊደርስ የሚችለውን ተጨማሪ ጫናን ይከላከላል" ሲል መንግሥት አስታውቋል።