ያልተከተቡ ስፖርተኞች በአውስትራሊያ የሜዳ ቴኒስ መወዳደር አይችሉም ተባለ

የኮሮናቫይረስ ክትባት ያልወሰዱ የሜዳ ቴኒስ ተጫዋቾች በ2022ቱ የአውስትራሊያ ኦፕን ላይ እንዲወዳደሩ አይፈቀድላቸውም ሲሉ የውድድሩ ዳይሬክተር ክሬግ ቲሊ ተናግሩ።
ከቅርብ ወራት ወዲህ የአውስትራሊያ ፖለቲከኞች የሚሰጡት ተቃራኒ አስተያየት ጉዳዩን ግራ አጋቢ አድርጎት ነበር።
በ2021 በወንዶች ዘርፍ አሸናፊ የሆነው ኖቫክ ጆኮቪች ስለ ክትባቱ ሁኔታ በይፋ መግለጽ እንደማይፈልግ ተናግሯል።
"ኖቫክ ለመጫወት መከተብ እንዳለበት ያውቃል።መጥቶ ቢጫወት ደስ ይለናል" ብለዋል ቲሊ።
"በሚቀጥለው የፈንጆቹ ዓመት በሜልበርን ከጥር 17 አስከ 30 የሚካሄደው ውድድር ሙሉ ተመልካች ባለበት እንደሚካሄድ ቲሊ አረጋግጠዋል።
ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የቴኒስ ተጫዋቾች አልተከተቡም። እስከ ጥቅምት ወር መጨረሻ በዓለም አቀፉ የቴኒስ ማኅበር ዘርፍ ከተወዳደሩ ወንዶች 35 በመቶ ያህሉ ያልተከተቡ ነበሩ።
የሴቶች ቴኒስ ማኅበር በተጫዋቾቹ ዘንድ ያለውን የክትባት መጠን ለቢቢሲ ስፖርት ይፋ አላደረገም።
የሴቶች ቴኒስ ማኅበር ሁሉም ተወዳዳሪዎች ወደ ሜልቦርን መጓዝ እንደሚችሉ ማወቁን የሚገልጽ ደብዳቤ ለተጫዋቾች በጥቅምት ወር ልኳል።
በደብዳቤው አክሎም ሁሉም ተጫዋቾች (ተከተቡም አልተከተቡም) በጉዟቸው 72 ሰዓታት ውስጥ ቫይረሱ እንደሌለባቸው የሚያሳይ ማስረጃ ማሳየት አለባቸው ብሏል።
ሆኖም የቪክቶሪያ ግዛት አስተዳዳሪ ዳንኤል አንድሪውዝ በጥቅምት ወር ያልተከተበ የቴኒስ ተጫዋች ወደ አውስትራሊያ ለመግባት ቪዛ ይሰጠዋል ብለው እንደማያስቡ ገልጸዋል።
ወረርሽኙ ከተከሰተ በኋላ አውስትራሊያ በጉዞ እና በእንቅስቃሴ ላይ አንዳንድ ጥብቅ ገደቦች አሳልፋለች።
ለ2021 ውድድር የተጓዙ ተጫዋቾች፣ ባለስልጣናት እና ደጋፊ ሠራተኞች አውስትራሊያ ሲደርሱ ለ14 ቀናት በለይቶ ማቆያ እንዲቆዩ ተገደዋል።
አንዳንዶች አብረዋቸው በተጓዙት ላይ የኮሮናቫይረስ ከተገኙኘ በኋላ ክፍላቸውን ለቀው እንዲወጡ አልተፈቀደላቸውም ነበር። በዚህም በክፍላቸው ውስጥ ጊዜያዊ ልምምዶችን እንዲያደርጉ አስገድዷቸዋል።












