በኦሮሚያ ክልል ተጥሎ የነበረው የሰዓት እላፊ ገደብ እንዲነሳ ተደረገ

የፎቶው ባለመብት, ADAMA CITY BDK
በአገሪቱ ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ከቀናት በፊት በኦሮሚያ ክልል ተጥሎ የነበረው የሰዓት እላፊ ገደብ መነሳቱን የክልሉ ዐቃቤ ሕግ አሳወቀ።
ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በመላው የክልሉ አካባቢዎች ተግባራዊ እንዲሆን ወጥቶ የነበረው በምሽት የክልሉ ነዋሪዎችና ተሽከርካሪዎች በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ላይ የሰዓት ገደብ የሚጥል ዕገዳ ተጥሎ ነበር።
ነገር ግን የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ወይዘሮ አዱኛ አሕመድ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደገለጹት ተጥሎ የነበረው ከምሽት አስከ ንጋት የሚቆየው የእንቅስቃሴ ገደብ ለጊዜው መነሳቱን አስታውቀዋል።
የሰዓት እላፊ ገደብ መጣሉን ተከትሎ የኦሮሚያ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ግዛቸው ገቢሳ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ በክልሉ የሰዎችና የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴን በመለየት ከምሽቱ 2 ሰዓት እስከ ንጋቱ 11፡30 ድረስ እንቅስቃሴ ማድረግ ተከልክሎ ነበር።
በዚህም መሠረት ሰዎች መንቀሳቀስ የሚችሉት ከንጋቱ 11፡30 እስከ ምሽቱ 3 ሰዓት የነበረ ሲሆን ተሸከርካሪዎች ግን ከንጋት 11፡30 እስከ ምሽቱ 2 ሰዓት ድረስ ብቻ እንዲንቀሳቀሱ ተወስኖ ተግባራዊ ሲደረግ ነበር።
የኦሮሚያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ወ/ሮ አዱኛ እንደገለጹት በክልሉ ተጥሎ የነበረው የሰዓት እላፊ ገደብ እንዲነሳ የተደረገው፣ እስካሁን በተከናወኑ ተግባራት የተሻለ ውጤት በመገኘቱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም በሰዓት እላፊ ገደቡ ሳቢያ በክልሉና በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ጫና እንዳይፈጠር ለማድረግ ውሳኔው እንዲነሳ መደረጉን አመልክተዋል።
ቀደም ሲል የተጣለው የሰዓት እላፊ ገደብ እንዲነሳ ቢደረግም በቀጣይ የሚኖሩ ሁኔታዎች እየተገመገሙ የሰዓት እላፊ ገደቡ እንደገና በመላው ክልሉ ወይም እንደየ አካባቢዎች ሁኔታ እየተለየ ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችል ዐቃቤ ሕጓ ገልጸዋል።
በሰዓት እላፊው አማካይነት ተጥሎ የነበረው የእንቅስቃሴ ገደብ ለጊዜው የተነሳ ቢሆንም "አስፈላጊ የደኅንነት ፍተሻ በተለያዩ የፀጥታ አካላት እና በሕዝባዊ አደረጃጀት አማካይነት ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል።
በትግራይ የተቀስቀሰው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወደ አጎራባች የአማራ እና አፋር ክልሎች መስፋፋቱን ተከትሎ የፌደራል መንግሥቱ በመላ አገሪቱ ተፈጻሚ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የደነገገ ሲሆን በዚህ ውስጥም ሰዓት እላፊ ገደብም ሊጣል እንደሚችል አመልክቶ ነበር።














