የአሜሪካ መንግሥት ግዙፉን የመሠረተ ልማት ወጪ አጸደቀ

ጆ ባይደን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላትን ለወራት ሲያጨቃጭቅ የነበረው የአሜሪካ የመሠረተ ልማት ረቂቅ ሰነድ፣ ከብዙ ክርክር በኋላ ሕግ ሆኖ ጸደቀ።

ረቂቁን ፊርማቸውን በማኖር ሕግ እንዲሆን ያጸደቁት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ናቸው።

ይህ በትውልድ አንድ ጊዜ ብቻ ይጸድቃል የሚባልለትና እጅግ ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል የተባለው የመሠረተ ልማት ረቂቅ ሰነድ ከ2 ሺህ ገጾች በላይ ያሉት ሰነድ ሲሆን፣ አሜሪካ በሚመጡት አሥርታት ለመሠረተ ልማት የምታወጣቸውን ከፍተኛ ወጪዎችን የያዘ መዘርዝር ነው።

ይህ ሰነድ ሕግ ሆኖ መጽደቁ በቅርብ በቨርጂኒያ ግዛት የአስተዳዳሪ ምርጫ ያልተጠበቀ ሽንፈት ለገጠማቸው ዲሞክራቶች ትልቅ ድል ነው ተብሏል።

መጪው ትልውድ ይህን ሰነድ አሜሪካ የስኬት ጉዞ የጀመረችበት ሲል ይዘክረዋል ብለዋል ጆ ባይደን።

"አሜሪካዊያን ልነግራችሁ የምፈልገው ሕይወታችሁ መቀየር ይጀምራል። አሜሪካ በድጋሚ መመንደግ ጀምራለች" ሲሉም ጆሴፍ ባይደን በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት ንግግር አድርገዋል።

ይህ ሕግ በሚቀጥሉት ስምንት ዓመታት የፌዴራሉ መንግሥት ለመሠረተ ልማት እጅግ ግዙፍ መዋዕለ ነዋይ እንዲያፈስ የሚፈቅድለት ነው።

በዚህ የመሠረተ ልማት ግዙፍ ፕሮጀክት በመላው አሜሪካ ግዙፍ ድልድዮች ይጠገናሉ፣ አውራ ጎዳናዎች ይታደሳሉ፣ የባቡር መንገዶችና መስመሮች በዘመናዊ መልክና በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ይሳለጣሉ፣ የኢንተርኔትና ሌሎች የመሠረተ ልማት አውታሮች ከፍተኛ ወጪ ተመድቦላቸው ይስፋፋሉ።

የመርከብ ወደቦችና አየር መንገዶችም በከፍተኛ ሁኔታ ይጠገናሉ ይዘምናሉ ተብሏል።

ለኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያዎች ግንባታ ብቻ በዚህ ሰነድ አሜሪካ በቀጣይ ዓመታት ከ7 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ እንደምታደርግ ይጠበቃል።

ከዚህም ባሻገር ንጹህ የመጠጥ ውሃ፣ ከፍተኛ ፍጥነት ያለው የብሮድባንድ ኢንተርኔት፣ አገር አቀፍ የኤሌክትሪክ መስመሮች፣ እንዲሁም በኤሌክትሪክ ለሚሰሩ መኪናዎች ጉልበት የሚሞሉበት (ቻርጅ የሚያደርጉባቸው) ጣቢያዎች በስፋት ይገነባሉ።

የፌዴራል መንግሥቱ በታሪኩ እንዲህ ዓይነት ከፍተኛ የመሠረተ ልማት ወጪ ሲያወጣ ይህ የመጀመርያው ነው ተብሏል።

ይህ ሰፊ የመሠረተ ልማት ወጪ ከየት በሚመጣ ገንዘብ ነው የሚደጎመው የሚለው ብዙ ያነጋገረ ሲሆን፣ በዋናነት ለኮቪድ የአስቸኳይ ጊዜ ፈንድ ተብሎ የተያዘና፣ ሆኖም ግን እስከዛሬ ወጪ ያልተደረገ ተጠባባቂ ገንዘብ፣ ከክሪፕቶከረንሲ ከሚገኝ ግብር ገቢ እና ሌሎች የገንዘብ ምንጮች ይኖራሉ ተብሏል።

ያም ሆኖ ይህ ግዙፍ ወጪ በአሜሪካ የፌዴራል መንግሥቱን የበጀት ሚዛንን ሊያዛባ እንደሚችል ተገምቷል።

የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ይህን ረቂቅ ለማጽደቅ ሦስት ወራትን ወስዶበታል።