ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ በታይዋን ጉዳይ 'በእሳት እየተጫወተች ነው' ሲሉ ዢ ባይደንን አስጠነቀቁ
የቻይናው ፕሬዝደንት ዢ ጂንፒንግ ታይዋን ሉዓላዊ አገር እንድትሆነ ማበረታታት "በእሳት እንደመጫወት ነው" ሲሉ የአሜሪካውን ፕሬዝደንት አስጠነቀቁ።
ባይደን ከቻይናው አቻቸው ዢ ጂንፒንግ ጋር በበየነ መረብ ውይይት ያደረጉ ሲሆን ይህም ባይደን ወደ ሥልጣን ከመጡ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ከውጭ አገር መሪ ጋር ያደረጉት ውይይት ነው ተብሏል።
ከሁለቱ መሪዎች ዋነኛ አጀንዳ መካከል የታይዋን ጉዳይ ቀዳሚው ነው።
በቻይና መንግሥት የሚተዳደረው ግሎባል ታይምስ በሁለቱ መሪዎች ውይይት ላይ ዢ በቅርቡ "የታይዋን ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ የሉዓላዊነት አጀንዳን ለማራመድ የአሜሪካንን ድጋፍ ለማግኘት ማማተራቸውን ተከትሎ ለተፈጠረው ውጥረት" አሜሪካንን ተጠያቂ አድርገዋል ሲል ዘግቧል።
ዢ "እንዲህ አይነት ውሳኔዎች እጅግ አደገኛ ናቸው፤ ልክ በእሳት እንደመጫወት። ማንም በእሳት ቢጫወት መቃጠሉ አይቀርም" ስለማለታቸው ተዘግቧል።
ዋይት ሐውስ በበኩሉ ፕሬዝደንት ባይደን በታይዋን ሰርጥ ሰላም እና አለመረጋጋት እንዳይኖር ምክንያት ሊሆኑ አይችልም ብሏል።
ቻይና፣ ታይዋን እና አሜሪካ
ቻይና ታይዋንን እንዳመጸኛ አንዲት ግዛቷ አድርጋ ነው የምትመለከታት ሲሆን ታይዋን ግን ራሷን እንደ አንድ ሉዓላዊት አገር ነው የምትቆጥረው። አሜሪካ ደግሞ ታይዋን እራሷን እንድትከላከል ለመርዳት የሚያስችላት ሕግ አላት። ይህ ሕግ ግን ሆነ ተብሎ ግልጽ እንዳይሆን ተደርጓል።
በዚህም ቻይና ታይዋንን ብታጠቃ የአሜሪካ ምላሽ በትክክል ምን ሊሆን እንደሚችል ግልጽ አይደለም።
ፕሬዝደንት ባይደን ከሳምንታት በፊት ቻይና ታይዋንን ብታጠቃ አሜሪካ ከታይዋን ጎን ቆማ ትከላከላለች በማለት መናገራቸው ይታወሳል።
• ቻይና እና ታይዋን ለምን ደካማ ግንኙነት ኖራቸው? በአውሮፓውያኑ 1940 ዎቹ ቻይና እና ታይዋን በእርስ በእርስ ጦርነት ነበር የተከፋፈሉት። ነገር ግን ቻይና አሁንም ቢሆን ደሴቲቷ አስፈላጊ ከሆነ በኃይልም ቢሆን ትመለሳለች የሚል እምነት አላት።
• ታይዋን የምትተዳደረው እንዴት ነው? ደሴቲቱ የራሷ ሕገ መንግሥት፣ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ መሪዎች እና 300 ሺህ ገደማ የሚሆኑ የሠራዊት አላት።
•እንደ አገር ለታይዋን ማን እውቅና ሰጣት? ለታይዋን ዕውቅና የሰጧት ጥቂት አገሮች ብቻ ናቸው። በርካታዎቹ ቤጂንግን መቀመጫ ላደረገው የቻይና መንግሥት እውቅና ይሰጣሉ። አሜሪካ ከታይዋን ጋር ኦፊሴላዊ ግንኙነት የላትም ነገር ግን ደሴቲቱ እራሷን ለመከላከል የሚያስችል ድጋፍ እንድትሰጥ የሚጠይቅ ሕግ አላት።
ምንም እንኳ ሁለቱ መሪዎች ታይዋንን በተመለከተ ጠንከር ያሉ ቃላቶችን ቢለዋወጡም ስብሰባቸውን ሲጀምሩ ሞቅ ያለ ሰላምታ ተለዋውጠው መሆኑ ተገልጿል። በውይይታቸው ጀማሮ ላይ፤ ዢ "የቀድሞ ወዳጄን" ስላየሁ ደስተኛ ነኝ በማለት ስለ ባይደን ተናግረዋል።
ባይደን በበኩላቸው ከዢ ጋር "ሁልጊዜም በግልጽ" እንደሚነጋገሩ ተናግረዋል።
ዢ ሁለቱ አገራት "ተግባቦታቸውን" ማሻሻል እንዳለባቸው እና የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን "አብረው መጋፈጥ አለባቸው" ብለዋል።
ሁለቱ መሪዎች በምን ተጨማሪ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ?
በንግድ ጉዳይ ላይ ፕሬዝደንት ባይደን አሜሪካውያን ሠራተኞች እና ኢንደስትሪዎች አግባብ ካልሆነው የቻይና የንግድ ሥርዓት መጠበቅ አለባቸው ብለዋል።
ዢ ጂንፒንግ በበኩላቸው አሜሪካ "በብሔራዊ ደኅንነት ስም የቻይና ኩባያዎችን መበዝበዝ ማቆም አለባት" ስለማለታቸው ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ባይደን እና ዢ ለሦስት ሰዓታት በዘለቀው ውይይታቸው በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ላይም ተነጋግረዋል።