ስቴቨን ጄራርድ የአስተን ቪላ አሰልጣኝ ሆኖ ተሾመ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቀድሞ የሊቨርፑል እና የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አማካይ ስቴቨን የአስቶን ቪላ ክለብ አሰልጣኝ ሆኖ ተሾመ።
ጄራርድ ክለቡን ለሦስት ዓመት ተኩል ለማሰልጠን ውል መያዙ አስተን ቪላ ክለብ ይፋ አድርጓል።
የ41 ዓመቱ ጄራርድ የአስተን ቪላ ክለብ ኃላፊነትን ከመቀበሉ በፊት ለሦስት ዓመታት የስኮትላንድ ክለብ የሆነውን ሬንጀርስን ሲያሰለጥን ቆይቷል።
ጄራርድ ሬንጀርስ በባለፈው የውድድር ዘመን ከ10 ዓመታት በኋላ የሊጉን ዋንጫ እንዲያነሰ ረድቶ ነበር።
ዕሁድ ዕለት አስተን ቪላ አምስት ዓመት በክለቡ የቆዩትን አሰልጣኝ ዲን ስሚዝን ከሥራ ማሰናበቱ ይታወሳል።
አስተን ቪላ በአሁኑ ወቅት በፕሪሚየር ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ላይ ከወራጅ ቀጠና በሁለት ነጥቦች ብቻ ርቀው 16ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
"አስተን ቪላ በእንግሊዝ እግር ኳስ ውስጥ ብዙ ታሪክ እና ባህል ያለው ክለብ ነው፤ አሰልጣኝ በመሆኔ ትልቅ ክብር ተሰምቶኛል" ብሏል ጄራርድ ከሹመቱ በኋል።
ጄራርድ የበላይ የአሰልጣኝነት ሥራውን የጀመረው የኮቲሹን ሬንጀርስ ክለብ እአአ 2018 ላይ ማሰልጠን በጀመረበት ወቅት ነው።
ጄራርድ ወደ ቪላ መሄዱን ተከትሎ አስተን ቪላ ለስኮትላንዱ ክለብ 4.5 ሚሊዮን ፓዎንድ ካሳ እንደሚከፍል ተዘግቧል።
በእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን እና በሊቨርፑል ክለብ ውስጥ ትልቅ ስም የገነባው ጄራርድ፤ ለሊቨርፑል 710 ጊዜ ተሰልፎ ተጫውቷል። ለእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ደግሞ 114 ጊዜ ተሰልፎ ተጫውቷል።
ጄራርድ የአስተን ቪላ አሰልጣኝነት ሥራውን ከተረከበ በኋላ ብራይተንን በሜዳው ያስተናግዳል። ቀጥሎም ኃያሎቹን ማንችስተር ሲቲ፣ ሊቨርፑል እና ቼልሲን ይገጥማል።












