የፖላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ለስደተኞች ችግር ፑቲንን ተጠያቂ አደረጉ

ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል

የፖላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር አገራቸውን ከቤላሩስ ጋር በሚያዋስነው ድንበር ላይ ለተፈጠረው የስደተኞች ቀውስ የሩሲያውን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን ከሰሱ።

ማቲየዝ ሞራዊኪ እንዳሉት የፑቲን አጋር የሆኑት የቤላሩሱ አምባገነን መሪ ቀውሱን እያቀነባበሩ ቢሆንም "ዋናው ጠንሳሹ ያለው ሞስኮ ነው" ብለዋል።

ቢያንስ 2,000 ስደተኞች በከፍተኛ ቅዝቃዜ ውስጥ ድንበር ላይ ይገኛሉ።

የቤላሩሱ መሪ አሌክሳንደር ሉካሼንኮ የአውሮፓ ሕብረት ማዕቀብ ለመበቀል ሰዎችን ወደ ድንበር እየላኩ ነው የሚለውን ክስ አስተባብለዋል።

የቪዲዮ ምስሎች በቤላሩስ በኩል ባለው እና በሽቦ በታጠረው የፖላንድ ድንበር ብዙ ሰዎችን አስመልክተዋል። ጥቂቶች መቁረጫዎችን ተጠቅመው፣ ሌሎች የዛፍ ግንዶችን እና የቡድን ኃይልን ተጠቅመው ለማቋረጥ ሲሞክሩ የፖላንድ ጠባቂዎች ደግሞ አስለቃሽ ጭስ በሚመስል ነገር ሲከላከሏቸው ታይተዋል።

ከስደተኞቹ መካከል ብዙዎቹ ወጣት ወንዶች ቢሆኑም በተለይም ከመካከለኛው ምሥራቅ እና እስያ የመጡ ሴቶች እና ህጻናትም ይገኙባቸዋል።

በድንበሩ ስፍራ ቅዝቃዜው ከዜሮ በታች ስለሚወርድ በቅርብ ሳምንታት የብዙ ሰዎች ሕይወት አልፏል።

የፖላንድ ጠቅላይ ሚንሰትር "ሉካሼንኮ እየፈጸመው ያለው ይህ ጥቃት ዋና ሃሳቡ የሚመነጨው ከሞስኮ ነው። ዋናው ጠንሳሽ ደግሞ ፕሬዝዳንት ፑቲን ናቸው" ብለዋል።

የሩሲያ እና የቤላሩስ መሪዎች ስደተኞች በቤላሩስ በኩል እንዲጓዙ እና ወደ አውሮፓ ህብረት እንዲገቡ በመፍቀድ ህብረቱን ለማተራመስ እየሞከሩ ነው ሲሉ ከሰዋል።

የአውሮፓ ህብረት አባል ወደሆኑት ፖላንድ፣ ሊትዌንያ እና ላቲቪያ ባለፉት ወራት ከቤላሩስ በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሃገራቸው ለመግባት የሚሞክሩ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል። ሊትዌንያ ከቤላሩስ ጋር በሚያዋስናት ድንበር ላይ ማክሰኞ እከሉ ለሊት ጀምሮ የሚተገበር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጃለች።

ፖላንድ የዓለም አቀፍ የጥገኝነት ህግጋትን በሚጻረር መልኩ ስደተኞችን ወደ ቤላሩስ ድንበር ወደ ኋላ በመግፋት ተከሳለች።

የ33 ዓመቱ ኢራቃዊው ሽዋን ኩርድ ለቢቢሲ በስልክ "ማንም ሰው የትም እንድንገባ አይፈቅድልንም" ብሏል።

"ማምለጫ መንገድ የለም። ፖላንድ እንድንገባ አትፈቅድም። ማታ ማታ ሄሊኮፕተሮችን ያበረራሉ። እንቅልፍ አያስተኙንም። በጣም ይርበናል። እዚህ ምንም ውሃም ሆነ ምግብ የለም። ህጻናት ልጆች፣ አዛውንቶች እና ሴቶች አሉ" ብሏል።

ሊትዌንያ በበኩሏ ስደተኞች ሊጎርፉ ይችላሉ በሚል ስጋት ሊትዌንያ ወታደሮቿን ወደ ቤላሩስ ድንበር አስጠግታለች።

ስደተኞች በቤላሩስ እና ፖላንድ ድንበር ላይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቤላሩስስ ምን አለች?

ሉካሼንኮ ከቤላሩስ መንግስት የዜና ወኪል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በድንበር ዙሪያ ሩሲያን ወደ ግጭት ሊያስገባ የሚችል ማንኛውንም ወታደራዊ ግጭት ለማስወገድ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

"እብድ አይደለሁም" ሲሉ አደጋውን እንደሚያውቁ ተናግረው ነገር ግን "አንበረከክም" በማለት ሃሳባቸው ገልጸዋል።

የቤላሩስ መከላከያ ሚኒስቴር ዋርሶው በሺህዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን ወደ ድንበር በማስጠጋት ስምምነቶችን ጥሳለች ሲል ከሷል።

ሩሲያ የድንበር ሁኔታውን በተመለከተ አጋሯ የወሰደችውን "ኃላፊነት" በማድነቅ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተልኩ ነው ብላለች።