የሱዳን ፖሊስ መንፈንቅለ መንግሥቱን ለመቀወም አደባባይ በወጡት ላይ አስለቃሽ ጭስ ተኮሰ

ታትሟል

የሱዳን የጸጥታ ኃይሎች በመዲናዋ ካርቱም ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ይቋቋም በሚል የተቃውሞ ሰልፍ የወጡ ዜጎች ላይ አስለቃሽ ጭስ መተኮሳቸው ተሰምቷል።

በተቃውሞ ሰልፉ እየተሳተፉ የሚገኙ በርካታ መምህራንም በጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ሌሊቱን ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ተቃዋሚዎች ለሁለት ቀናት የሚቆየውን ጫና የማሳደር እንቅስቃሴ ለማጠናከር ጎማዎችን በማቃጠል እና ድንጋይ በመጠቀም የተለያዩ መንገዶችን ዘግተዋል።

ጥያቄያቸውም በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን የያዘው ወታደራዊ መንግሥት በሰላማዊ መንገድ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም መንገዱን ይክፈት የሚል ነው።

የአረብ ሊግ አገራት መሪዎች መፈንቅል መንግሥቱን ካደረጉት ወታደሮች ጋር ድርድር ለማድረግ ወደ መዲናዋ ካርቱም መግባታቸውን ተከትሎ ነው ሰልፈኞች በድጋሚ ወደ አደባባይ መውጣት የጀመሩት።

ከመጀመሪያው መፈንቅለ መንግሥት በኋላ በጠቅላይ ሚንስትርነት የተመረጡት አብደላ ሀምዶክ በአሁኑ ሰዓት በቤታቸው የቁም እስረኛ ሆነው የሚገኙ ሲሆን ወታደሮቹም አብረዋቸው እንዲሰሩ ጫና እያሳረፉባቸው ስለመሆኑ ተዘግቧል።

ባለፈው ወር የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ ጀነራል አብደል ፈታህ አል ቡርሀን መንግሥት ከሲቪሎች ጋር ስልጣን ለመጋራት ያደረገውን ስምምነት ያፈረሱ ሲሆን በርካታ የሲቪል መሪዎችንም በቁጥጥር ስር አውለዋል። አስከትለውም በአገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጀዋል።

ምንም እንኳን በአገሪቱ ባለው የኢንተርኔ መቆራረጥ ምክንያት በርካታ ሰዎች የሁለት ቀን የተቃውሞ ሰልፍ መጠራቱን ያልሰሙ ቢሆንም ጥቂት የማይባሉ መምህራን ግን በትምህርት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በር ላይ በመሰባሰብ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

"ጀነራሉ የወሰዱትን እርምጃ ለመቃወም በዝምታ የታጀበ ሰልፍ በሚኒስቴሩ በር ላይ አካሂደናል" ሲል ሞሀመድ አል አሚን የተባለው መምህር ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግሯል።

"ትንሽ ቆይቶ ግን ፖሊስ መጥቶ አስለቃሽ ጭስ መተኮስ ጀመረ። እኛ ምንም አላደረግንም ነበር። በዝምታ መንገድ ላይ በመቆም የጽሁፍ መልእክቶችን ነበር ያስተላለፍነው። ለምን አስለቃሽ ጭስ እንደተተኮሰብን አላውቅም" ብሏል።

በሰሜናዊ የካርቱም ክፍል የጸጥታ ኃይሎች ዋና ዋና መንገዶችን በጥብቅ እየተቆጣጠሩ ሲሆን አስለቃሽ ጭስ፣ ፈንጂዎችና ዱላዎችን ይዘው እንደሚንቀሳቀሱ ሮይተርስ ዘግቧል።

አብዛኛው የካርቱም ነዋሪ በአሁኑ ሰዓት ቁጣ ላይ መሆኑን ቢቢሲ ተዘዋውሮ ማስተዋል ችሏል። በርካቶችም ወደ መንደራቸው የሚወስዱ መንገዶችን በመዝጋት ተቃውሟቸውን እየገለጹ ነው።

ምንም እንኳን ከሁሉም አቅጣጫ የተቃውሞ ድምጾች እየተሰሙ ቢሆንም ወታደራዊው መንግሥት ግን ምንም ስህተት እንዳልሰራ እየገለጸ ነው።

"ይህ መፈንቅለ መንግሥት እንዳልነበረ በጊዜ ብዛት የሚታይ ይሆናል። የሲቪል መንግሥት መስርተን ምርጫም እንዲካሄድ አናደርጋለን" ብለዋል አድሚራል ፋታህ አል ራህማን።