በአሜሪካ በአንድ የሙዚቃ ፌስቲቫል ላይ በደረሰ አደጋ ስምንት ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች ቆሰሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአሜሪካዋ ቴክሳስ ሂዩስተን ውስጥ በአንድ የሙዚቃ ፌስቲቫል መክፈቻ ላይ በታደሙ ሰዎች መካከል በተፈጠረ መጨናነቅና ግፊያ ቢያንስ የስምንት ሰዎች ህይወት በርካቶች ላይ ጉዳት መድረሱ ተነገረ።
የአደጋ ጊዜ ባለሥልጣናት እንደተናገሩት በፌስቲቫሉ ላይ በታደሙት በርካታ ሰዎች ወደ መድረኩ ለመቅረብ በተፈጠረ መገፋፋት መጨናነቅ ተፈጥሮ ነው አደጋው የደረሰው።
በዚህም ሳቢያ ስምንት ሰዎች ሲሞቱ አስራ አንድ ሰዎች ደግሞ የልብ ድካም ገጥሟቸው ወደ ሆስፒታሎች ተወስደዋል።
በዚህ 50 ሺህ ያህል ሰው በታደመበት ዝግጅት ላይ ከሞቱትና ከባድ ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች በተጨማሪም 300 የሚሆኑ ሰዎች ቀላል የመቁሰልና የመላላጥ ጉዳት ደርሶባቸው ህክምና እንደተደረገላቸው ተነገሯል።
የሁዩስተን እሳት አደጋ መሥሪያ ቤት ኃላፊ የሆኑት ሳሙኤል ፔኛ እንደተናገሩት አደጋው ያጋጠመው አርብ ምሽት ከሦስት ሰዓት በኋላ ነበር።
"የተሰበሰበው ሕዝብ ወደ መድረኩ ለመጠጋት በሚገፋፋበት ጊዜ መጨናነቅና መደናገጥ ተፈጥሯል" ሲሉ ኃላፊው ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
የተፈጠረው መጨናነቅና መረጋገጥ በሰዎች ላይ ጉዳት ሲያስከትል ከባድ መረበሽ ተፈጥሮ ጉዳት አስከትሏል ሲሉም ተናግረዋል ሳሙኤል ፔኛ።
የፌስቲቫሉ መስራች የሆነው ትራቪስ ስኮት ለአንድ ጋዜጣ እንደተናገረው ለ75 ደቂቃዎች መድረክ ላይ ሆኖ ሙዚቃውን ባቀረበበት ጊዜ ከተመልካቾች መካከል የስቃይ ድምጽ ይሰማ ስለነበረ በተደጋጋሚ ለማቋረጥ ተገዶ ነበር።
የራፕ ሙዚቃ አቀንቃኙ የደኅንነት ሠራተኞች ተመልካቾቹ ደህና መሆናቸውን እንዲያረጋግጡና እርዳታ እንዲሰጡ ጠይቆ ነበር።
የዝግጅቱ አስተባባሪዎች በበርካታ ተመልካቾች ላይ ጉዳት መድረሱ ሲታወቅ የሙዚቃ ፌስቲቫሉ እንዲቋረጥ አድርገዋል። ወዲያውኑም በመጨናነቁ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥር በፍጥነት በመጨመሩ በስፍራው የአስቸኳይ ጊዜ ህክምና ለመስጠት ከተሰማሩት ባለሙያዎች በላይ ሆኖ እንደነበር ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
ዝግጅቱ ከመጀመሩ በፊት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በዝግጅቱ ስፍራ የፍተሻ አካባቢዎችን ጥሰው ገብተው እንደነበር የአካባቢው መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ከአርብ ጀምሮ ለሁለት ተከታታይ ቀናት እስከ ቅዳሜ ሊካሄድ ዕቅድ ተይዞለት የነበረው በትራቪስ ስኮት የተዘጋጀው 'አስትሮ ዎርልድ' የተሰኘው የሙዚቃ ፌስቲቫል በተከሰተው አደጋ ምክንያት እንዲሰረዝ ተደርጓል።












