በኢትዮጵያና ታንዛኒያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ግጥሚያ የተከሰተው ምንድን ነው?

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የተቀባች ኳስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ኡጋንዳ እየተካሄደ በሚገኘው የሴካፋ ውድድር የኢትዮጵያ ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የታንዛኒያ አቻዋን 2 ለ1 ረትታለች።

የዚህ ጨዋታ ማብቂያ ግን እንደ ሌሎች ግጥሚያዎች ተጫዋቾች ተጨባብጠው የተለያዩበት አይደለም። ለመሆኑ የተፈጠረው ምንድን ነው?

ኢትዮጵያ ሰኞ ዕለት ባደረገችው የመጀመሪያው ጨዋታዋ ጅቡቲን 7 ለምንም መርታቷ ይታወሳል።

ቀጣይ ከጎረቤት ሃገር ኤርትራ ጋር ግጥሚያ የነበራት የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን 5 ለባዶ አሸንፋለች።

ሶስተኛው የኢትዮጵያ ጨዋታ ከታንዛኒያ ጋር ትናንት ረቡዕ በኡጋንዳ ንጄሩ የተደረገ ሲሆን የዚህ ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ ጎል አላስተናገደም።

በሁለተኛው አጋማሽ ተነቃቅታ የገባችው ኢትዮጵያ በ10 ደቂቃ ውስጥ ሁለት ጎል በማስቆጠር መሪነቱን ያዘች።

ሁለቱን የኢትዮጵያ ጎሎች መሳይ ተመስገንና ይየን ኒያቦኒ ናቸው ያስቆጠሩት።

ነገር ግን የታንዛንያዋ ሉቫንጋ አንድ ጎል አስቆጥራ የሃገሯን የጎል ዕዳ ወደ አንድ ዝቅ አደረገች። በዚህ ጎል የተነቃቁት ታንዛኒያዎች በተደጋጋሚ የጎል ማግባት ሙከራ ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም።

የጎል ሙከራቸውን የቀጠሉት ታንዛኒያዎች በጭማሪ ሰዓት ቅጣት ምት ያገኛሉ። ቅጣት ምቱ ወደ ጎል ከተሰነዘረ በኋላ የኢትዮጵያዋ ግብ ጠባቂ ቤቴልሄም በቀለ ኳሱን መቆጣጠር ባለመቻሏ የታንዛኒያዋ አጥቂ አይሻ ማሳካ ወደጎል ትቀይራታለች።

ነገር ግን ይህ ጎል ከጨዋታ ውጪ ነው በማለት የመስመር ዳኛዋ አሊዳ ኢራዱካንዳ ባንዲራቸውን ያውለበልባሉ።

በዚህ ውሳኔ ደስተኛ ያልሆኑት የታንዛኒያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አባላት ወደ መስመር ዳኛዋ በመሄድ ይከቧትና ይገፏት ጀመር።

የታንዛኒያዋ ተከላካይ ፉሙካዚ የመስመር ዳኛዋን ገፍትራ በመጣሏ በቀይ ካርድ ከጨዋታው ታግዳለች።

የታንዛኒያ ተጫዋቾች የመስመር ዳኛዋን በመግፋት በማዋከብ ብቻ ሳያልፉ ባንዲራዋን በመንጠቃቸው የካርድ ሰለባ ሆነዋል።

የጨዋታው ማብቂያ ፊሽካ ከተነፋ በኋላም የታንዛኒያ ተጫዋቾች የጨዋታውን ዳኞች በማዋከባቸው ከሴካፋ ቅጣት ይጠብቃቸዋል እየተባለ ነው።

በኡጋንዳ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ በምሕፃሩ ሴካፋ ከ20 ዓመት በታች ውድድር ባለፈው ቅዳሜ ነው የተጀመረው።

ታንዛንያ፣ ኤርትራ፣ ጅቡቲ፣ ኢትዮጵያ፣ ቡሩንዲና ኡጋንዳ እየተሳተፉ ሲሆን ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ሩዋንዳ፣ ኬንያና ሶማሊያ በውድድሩ አልተሳተፉም።

ኢትዮጵያ እስካሁን ያደረገቻቸውን 3 ጨዋታዎች በማሸነፍ በ9 ነጥብ ውድድሩን እየመራች ትገኛለች።

ሌላኛው በኡጋንዳ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ባለው ቀጣናዊው የእግር ኳስ ውድድር አነጋጋሪ የሆነው ጉዳይ 5 ኤርትራዊያን መጥፋታቸው ነው።

አምስቱ ተጫዋቾች ባለፈው ማክሰኞ ጠዋት ካረፉበት ሆቴል የተሰወሩ ሲሆን በሴካፋ ከ20 አመት በታች የሴቶች ሻምፒዮና የኤርትራ ብሄራዊ ቡድን አባል ነበሩ።

የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ እግር ኳስ ማህበራት ምክር ቤት ሴካፋ] ባወጣው መግለጫ ጉዳዩ ለፖሊስ ሪፖርት እንደተደረገና ምርመራም በመካሄድ ላይ መሆኑን ገልጻል።

ሴካፋ ከኡጋንዳ የእግር ኳስ ባለስልጣን ጋር የጠፉ ተጫዋቾችን ለማግኘት እንደሚሰራም ተናግረዋል።