ዋትስአፕ ከተጣለበት ቅጣት በኋላ በአውሮፓ የደኅንነት ፖሊሲውን ቀየረ

የፎቶው ባለመብት, PA Media
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ከመረጃ ጥበቃ ጋር በተያያዘ ከተጣለበት ከፍተኛ ቅጣት በኋላ ዋትስአፕ የደኅንነት ፖሊሲውን እንደገና እያስተካከለ ነው።
የተካሄደውን ምርመራ ተከትሎም የአየርላንድ የመረጃ ደኅንነት ጥበቃ ተቆጣጣሪ 225 ሚሊየን ዩሮ (190 ሚሊየን ፓውንድ) ቅጣት አስተላልፎበታል።
ቅጣቱ ከመረጃ ጥበቃ ቁጥጥር (ጂዲፒአር) ጋር በተያያዘ የተጣለ በታሪክ ሁለተኛው ትልቁ ቅጣት ሲሆን ተቆጣጣሪው አካል ዋትስአፕ ፖሊሲዎቹን እንዲቀይርም ትዕዛዝ ሰጥቷል።
የአየርላንድ የመረጃ ጥበቃ ኮሚሽን መጀመሪያ ላይ ዋትስአፕ ከ30 ሚሊየን አስከ 50 ሚሊየን ዩሮ ቅጣት አቅርቦበት ነበር።
ይሁን እንጂ በአሰራሩ መሠረት ከሌሎች የአውሮፓ ሕብረት አገራት ተቆጣጣሪዎች ጋር ከተማከረ በኋላ መጠኑን እንደገና ገምግሞታል።
እስካሁን ከጠቅላላ የመረጃ ጥበቃ ቁጥጥር ጋር በተያያዘ ከፍተኛው ቅጣት የተጣለበት አማዞን ነው። የተጣለበት ቅጣትም 636 ሚሊየን ዩሮ ነው።
ዋትስአፕ ለተጠቃሚዎች የሚያቀርበው አስፈላጊውን መረጃ እንደሆነ እንደሚያምን በመግለፅ በውሳኔው ላይ ይግባኝ ጠይቋል።
ዋትስአፕ ለተጣለበት ቅጣት ይግባኝ የጠየቀ ቢሆንም ፖሊሲዎቹን በአውሮፓ እና በዩናይትድ ኪንግደም እያሻሻለ ነው። ሆኖም በአገልግሎቱ ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ እንደማይኖር ገልጿል።
የፖሊሲ ማሻሻያዎቹ እየተደረጉ ያሉት ከነበረው አሰራር ላይ ዝርዝር ነገሮችን ለመጨመር እንደሆነና ይህም በሌሎች ዓለማት አገልግሎት ላይ ከሚውለው የዋትስአፕ ቅጂ (ቨርዥን) የተለየ በሆነውና በአውሮፓ ባለው የደኅንነት ፖሊሲ ላይ የሚቀርብ ነው ብሏል።
"በሒደቱም ሆነ ከተጠቃሚዎች ጋር በሚደረገው ስምምነት ምንም ለውጥ የለም። ተጠቃሚዎችም መተግበሪያውን ለመጠቀም እንደ አዲስ መስማማት ወይም ሌላ ነገር ማድረግ አይጠበቅባቸውም" ብሏል ድርጅቱ በአውሮፓ እያደረገ ያለውን የፖሊሲ ማሻሻያ በገለጸበት ወቅት።
ዋትስአፕ ያሻሻለው አዲሱ ፖሊሲው ወዲያውኑ ተግባር ላይ እንደሚውልም ገልጿል።












