የፌስቡክ አዲሱ ስም 'ሜታ' በእብራይስጥ ቋንቋ የያዘው ትርጉም መሳለቂያ ሆኗል

ማርክ ዙከርበርግ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ፌስቡክን ጨምሮ የተለያዩ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን የሚያስተዳድረው ኩባንያ ስያሜውን ወደ 'ሜታ' ከቀየረ በኋላ አዲሱ ስሙ አስራኤል ውስጥ መቀለጃ ሆኗል።

አዲሱ የፌስሙክ ስም 'ሜታ' የሚለው ቃል በእብራይስጥ ቋንቋ 'ሟች' የሚል ተቀራራቢ ትርጉሙ የያዘ በመሆኑ በአስራኤላውያን ዘንድ መሳለቂያ ሆኗል።

በዚህም ሳቢያ በርካታ ሰዎች #FacebookDead በሚል ሃሽታግ ትርጉሙን በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ እያጋሩ ነው።

'ዘካ' የተባለው ታዋቂ የአደጋ ጊዜ ነፍስ አድን በጎ ፈቃደኞች ቡድን በፌስቡክ አዲስ ስያሜ ላይ አሹፏል። ቡድኑ በትዊተር ገጹ ላይ "አትጨነቁ፣ [ልናድነው] እየሠራን ነው" በማለት አስፍረዋል።

ሌላው የትዊተር ተጠቃሚ ደግሞ "ሁሉም የእብራይስጥ ተናጋሪ የሚስቅበት ጥሩ ምክንያት ስለቀረበልን እናመሰግናለን" ብሏል።

ፌስቡክን ጨምሮ በርካታ የማኅበራዊ ትስስር መድረኮችን የያዘው ግዙፉ ተቋም ከባድ ትችት እየቀረበበት ባለበት በዚህ ወቅት የሁሉም መድረኮች አቃፊ የሆነውን ድርጅት ስያሜ 'ሜታ' የሚል አዲስ ስም መስጠቱ በዓለም ዙሪያ መነጋገሪያ ሆኗል።

ስያሜው በሌላ ቋንቋ ተተርጉሞ መሳለቂያ ሲሆን ፌስቡክ የመጀመሪያው አይደለም። በርካታ ኩባንያዎች በሌላ ቋንቋ አነጋጋሪ የሆነ ትርጉም ይይዛሉ። ታዋቂው ከዶሮ ሥጋ የሚዘጋጅ ምግቦችን የሚያቀርበው ምግብ ቤት ኬኤፍሲ አንዱ ነው።

እንደ አውሮፓውያኑ በ80ዎች ኬኤፍሲ በቻይና ሥራ ሲጀምር "ጣት ያስቆረጥማል'' የሚለው የንግድ መለያ ለቻይናውያን ተስማሚ አልነበረም።

የንግድ መለያ መሪ ሐሳቡ ተቀራራቢ ትርጉም "ጣቶችህን ብላ/ብይ" የሚል ሆኗል።

ሆኖም ትርጓሜው ኩባንያው ላይ ብዙም ተጽዕኖ አላሳደረም። በቻይና ትልቁ የፈጣን ምግብ አቅራቢ ድርጅት ነው።

ሮልስ ሮይስ የተሰኘው መኪና አምራች 'ሲልቨር ሚስት' ለተሰኘው መኪና የሰጠው ስያሜ በጀርመንኛ 'አይነ ምድር' የሚል ትርጉም ይይዛል።

በዚህም ምክንያት መኪናው 'ሲልቨር ሾዶ' ወደሚል ስያሜ ተቀይሯል።

የኖኪያ ምርት የሆነው 'ሉሚያ' በአንዳንድ የስፓኒሽ ተናጋሪዎች 'ሴተኛ አዳሪ' የሚል ትርጉም አለው።

ሆንዳ አንዱን ምርቱን 'ፊታ' ብሎ ለመሳየም ተዘጋጅቶ የነበረ ሲሆን፤ ትርጉሙ በስዊድንኛ 'የሴት ብልት' የሚል ትርጉም ስላለው የስያሜ ለውጥ አድርጓል።