ያደጉ አገራት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ትርፍ ክትባቶችን ለድሃ አገራት እንዲሰጡ ጥሪ ቀረበ

ክትባት ሲሰጥ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ከ160 በላይ የቀድሞ የዓለም መሪዎች እና ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎች የበለፀጉ አገራት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ትርፍ የኮቪድ ክትባቶችን ወደ ድሃ አገራት በፍጥነት እንዲያጓጉዙ ጥሪ አቀረቡ።

በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት በየቀኑ እየሞቱ የክትባቱ መባክን ሥነ ምግባር የጎደለው ነው ብለዋል።

በቀድሞው የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ጎርደን ብራውን በተዘጋጀ ደብዳቤ ነው ጥሪው የቀረበው።

ባለግዙፍ ኢኮኖሚዎቹ የጂ 20 አገራት በዚህ ሳምንት መጨረሻ በሮም የሚገናኙ ሲሆን ደብዳቤውም ለአዘጋጇ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ማሪዮ ተልኳል።

ደብዳቤውን ከፈረሙት መካከል 36ቱ የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች፣ 30ዎቹ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ሲሆኑ 100ዎቹ ደግሞ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ናቸው።

በዓለም ዙሪያ ከስድስት ቢሊዮን በላይ የኮቪድ ክትባት ዶዞች ተሰጥተዋል። ከዚህ ውስጥ 70 በመቶው የተሰጠው በጥቂት አገራት ነው። ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አገራት ውስጥ 2 በመቶዎቹ ሰዎች ብቻ ናቸው የተከተቡት።

አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ ዩኬ እና ካናዳ በዚህ ወር መጨረሻ 240 ሚሊዮን ጥቅም ላይ ያልዋሉ ክትባቶች እንደሚኖራቸው በደብዳቤው ተገልጿል። ክትባቶቹን በጣም ለሚያስፈልጋቸው አገራት በፍጥነት በአየር ሊይጓጉዙ ይችላሉ ተብሏል።

በየወሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተጨማሪ ክትባቶች ተጓጉዘው በአጠቃላይ 1.1 ቢሊዮን የሚሆኑት በአራት ወራት ውስጥ ሊሰጡ ይገባል ይላል ደብዳቤው።

ይህ ከሆነ የዓለም ጤና ድርጅት 70 በመቶ የሚሆኑ ጎልማሶች በሚቀጥለው ዓመት ወራት እንዲከተቡ የያዘው ዕቅድ ሊሳካ ይችላል ብሏል።

"ያለ ዝርዝር እቅድ 100 ሚሊዮን ክትባቶች በዓመቱ መጨረሻ ላይ ጥቅም ላይ የመዋያ ጊዜያቸው ያልፋል" ይላል ደብዳቤው።

"በፍጥነት እርምጃ ካልወሰድን ይህ አሃዝ በጥር 2022 መጨረሻ ወደ 200 ሚሊዮን ሊያደግ ይችላል።"

ዩናይትድ ኪንግደም በሚቀጥለው ዓመት ከ100 ሚሊየን በላይ ክትባት ለመለገስ ቃል ስትገባ ዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ 500 ሚሊየን ለመስጠት ቃል ገብታለች።

የጂ7 አገራት ቡድን በሰኔ ወር በዩኬ ባደረገው ስብሰባ ከ870 ሚሊዮን በላይ ክትባት ለመለገስ ቃል ገብቷል።

ክትባቶቹ በዋናነት የሚሰራጩት በኮቫክስ በኩል ሲሆን ይህም በዓለም ላይ ካሉት አገራት 20 በመቶ በጣም ተጋላጭ የሆኑትን ለመድረስ ያቀደ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ 30 በመቶ የሚሆነው ህዝቧን ሙሉ በሙሉ የከተበችው ኢንዶኔዥያ ፕሬዝዳንት የበለፀጉ አገራት ክትባቱን እንዲያካፈሉ አሳስበዋል ።

ጆኮ ዊዶዶ ለቢቢሲ "ሁሉም ረድተዋል። በእኔ አስተያየት ግን በቂ አይደለም" ሲሉ ተናግረዋል።

"በዚህ በችግር ወቅት ያደጉ አገራት ድሃ አገራት ክትባቶችን እንዲያገኙ በመርዳት ረገድ የበለጠ መስራት አለባቸው። በዚህም ይህን ወረርሽኝ በጋራ ማሸነፍ እንችላለን" ሲሉ ገልጸዋል።