የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር ሥልጣን ለቀቁ

የፎቶው ባለመብት, PA Media
ሰር ኪር ስታርመር ከዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትርነት እንዲሁም ከሌበር ፓርቲ መሪነት መልቀቃቸውን አስታወቁ።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ከሚገኝበት ዳውኒንግ ስትሪት ነምበር 10 ዛሬ በሰጡት መግለጫ ከሁለት ዓመት በፊት ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት መምጣታቸው "በሕይወቴ የሚያኮራኝ ቅጽበት ነው" ብለዋል።
ስታርመር ከባለቤታቸው ጋር ሆነው መግለጫውን ሲሰጡ ብዙዎች በጭብጨባ ድጋፋቸውን ሰጥተዋቸዋል።
ባለፈው ሳምንት አንዲ በርንሀም በግሬተር ማንችስተር ምርጫ ማሸነፋቸው የሌበሪ ፓርቲ መሪ በመሆን ስታርመርን እንዲገዳደሩ መንገድ ከፍቶላቸዋል።
ስታርመር ወደ ፖለቲካ የገቡት የሚሊዮኖችን ሕይወት በተሻለ ሁኔታ ለመለወጥ መሆኑን አስታውቀዋል።
በአውሮፓውያኑ ሐምሌ 2024 ሌበር ፓርቲ ወደ ሥልጣን እንደመጣም በንግግራቸው ይህንን ጠቅሰዋል።
የባለፈው ሳምንት የምርጫ ውጤት ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአንዲ በርንሀም መንገድ እንዲያመቻቹ ከሚኒስትሮቻቸው ጫና ውስጥ ከትቷቸዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም ጫና የበረታባቸው ኪር ስታርመር "ከጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው ይለቃሉ" በማለት በኃላፊነት የነበራቸውን ቆይታ ተችተዋል።
ዛሬ ጠዋት ከንጉሥ ቻርለስ ጋር በስልክ እንደተነጋገሩ እና ሥልጣን እንደሚለቅቁ እንዳሳወቋቸው ገልጸዋል።
"በአገሪቱ ትልቁን ሥራ" እየለቀቁ እንደሆነ ጠቅሰው በቀጣይ "እጅግ የሚጠቅመው ሥራ ላይ" እንደሚያተኩሩ ተናግረዋል።
"በቻልኩት መጠን ለሚስቴ ጥሩ ባል ሆኛለሁ። ባለቤቴ ከጎኔ በመቆም ጥሩ እና መጥፎም ጊዜ እንዳልፍ ረድታኛለች" ሲሉ በስሜት ተሞልተው ንግግራቸውን አሰምተዋል።
"ለውብ ልጆቼ ጥሩ አባት ሆኛለሁ፤ ልጆቼ የደስታዬ እና ኩራቴ ምንጭ ናቸው" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, PA Media
ስታርመር በተገቢው መንገድ ሥልጣን እንደሚያስረክቡ ገልጸው ለቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙሉ ድጋፋቸውን እንደሚሰጡ ተናግረዋል።
ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሁለት ዓመት በፊት ከነበረው አንጻር "ጠንካራ የሆነ እና ፍትሕ የሰፈነበት አገር" እንደሚረከቡ ማወቅ አለባቸው ብለዋል።
ከጎናቸው የነበሩ ጓደኞቻቸው እና የሥራ ባልደረቦቻቸውንም አመስግነዋል።

የፎቶው ባለመብት, PA Media
ስታርመር የተረከቡት ፓርቲ "በፖለቲካ፣ በፋይናንስ እና በሞራል የላሸቀ" እንደነበር ጠቅሰው በተደጋጋሚ "ፓርቲው አብቆታለታል" ሲባል መስማታቸውን በንግግራቸው ጠቅሰዋል።
ስታርመን እንዳሉት የሌበር ፓርቲያቸው ዋነኛ ጥያቄ እሳቸው በቀጣዩ ምርጫ ለመወዳደር የተሻሉት አማራጭ ስለመሆናቸው ነው።
ፓርቲያቸው ለዚህ ጥያቄ የሰጠውን ምላሽ አዳምጠው "በበጎ መንገድ" መቀበላቸውን አክለዋል።
እያንዳንዱ ውሳኔያቸው "የምወዳትን አገሬን በማስቀደም" የተወሰደ ነው ሲሉም ተደምጠዋል።

የፎቶው ባለመብት, PA Media















