የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ፓርቲ በምርጫው ማሸነፍ እና የአዲስ ግጭት ስጋት

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ምንም እንኳን ምርጫው የግጭት ጥላ ቢያጠላበትም፣ የጭቆና ክሶች ቢሰሙም እንዲሁም የተቃዋሚ ፓርቲዎች ተሳትፎ አናሳ ቢሆንም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ፓርቲ በአገሪቱ አጠቃላይ ምርጫ ከፍተኛውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ በማሸነፍ የበላይቱን ይዞ ለመቀጠል ችሏል።
ይፋ ከተደረጉት 501 መቀመጫዎች ውስጥ 438ቱን ያገኘው የብልጽግና ፓርቲ አዲስ መንግሥት ለመመሥረት ይችላል፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በቀጣይ ዓመት መስከረም በሥልጣናቸው ለመቀጠል ቃለ መሃላ ይፈጽማሉ። ይህ ለዐቢይ ደጋፊዎች ትልቅ ድል በመሆኑ በበላይነት የመሩትን የኢኮኖሚ ለውጥ እንደሚቀጥሉ ያምናሉ።
ነገር ግን ሌሎች ዐቢይ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ሲቀጥሉ በሕዝብ ብዛት በአፍሪካ ሁለተኛዋ በሆነችው አገር ውስጥ ያሉት ክፍፍል እና የደኅንነት ተግዳሮቶች እየተባባሱ ይሄዳሉ ብለው ይሰጋሉ።
የ49 ዓመቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሥልጣን የመጡት በአውሮፓውያኑ 2018 የተካሄዱ ተቃውሞዎችን ተከትሎ ሲሆን፣ መጀመሪያ ላይ ስለአንድነት ባደረጉት ጥሪ ከፍተኛ ተቀባይነትን ቢያገኙም፤ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የአገሪቱን መንግሥትን ተቆጣጥረው ከቆዩት ከትግራይ ፖለቲከኞች ጋር ተቃቅረዋል።
ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ ከአንድ ዓመት በኋላ በዋናነት ከኢትዮጵያ ሰሜናዊ ጎረቤት ከኤርትራ ጋር የነበረውን አስርታት ያስቆጠረ ፍጥጫን ለማስቀረት በወሰዱት እርምጃ ምክንያት የኖቤል የሰላም ሽልማትን አሸንፈዋል።
በአገሪቱ የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎች የሚካሄዱት ኃይለኛ የታጣቂዎች እንቅስቃሴ ስለማብቃታቸው ምልክቶች ባለማሳየታቸው የደኅንነት ባለሙያዎች አገሪቱ ወደ ጦርነት ልትመለስ እንደምትችል ይሰጋሉ።
በምርጫው ቀን፣ ከመንግሥት ኃይሎች ጋር የሚዋጉት ታጣቂ ቡድኖች በፈጠሩት የደኅንነት ስጋት ምክንያት በአገሪቱ በርካታ ሕዝብ በሚኖርባቸው ሁለቱ ክልሎች ውስጥ 143 የምርጫ ጣቢያዎች ሳይከፈቱ ቀርተዋል።
በአማራ ክልል የፋኖ ሚሊሻዎች እና በበሽብር ቡድንነት የተፈረጀው በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሰቀሰው የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ሁለቱም ምርጫውን እና ውጤቱን ውድቅ አድርገዋል።
ከአራት ዓመት በፊት ካበቃው የሁለት ዓመት የእርስ በርስ ጦርነት እያገገመ ባለው በትግራይ ክልልም ያለው ሁኔታ አሳሳቢ ነው። ጦርነት ዳግም ሊቀሰቀስበት ይችላል ተብሎ የሚሰጋበት ስድስት ሚሊዮን ነዋሪዎች ያሉት የትግራይ ክልል ምርጫ አልተካሄደበትም።
ትግራይ በሁለቱ ዓመት ጦርነት ወቅት ወታደሮቿ ከኢትዮጵያ መንግሥት ኃይሎችን ደግፈው ከተዋጉት ከኤርትራ ጋር ትዋሰናለች። ውድቅ ብታደርገውም በወታደሮቿ ትግራይ ውስጥ ሰፊ የሆነ ግፍ ፈጽመዋል ተብለው ይከሰሳሉ። ነገር ግን ጦርነቱ ካበቃ በኋላ የአዲስ አበባ እና የአሥመራ ግንኙነት በፍጥነት ተበላሽቷል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አገራቸው በ1985 ኤርትራ ነፃ አገር ስትሆን ኢትዮጵያ ያጣችውን የቀይ ባሕር ወደብን መልሳ ማግኘት እንዳለባት በተደጋጋሚ ሲናገሩ ቆይተዋል። ለዚህም 1,350 ኪ.ሜ የባሕር ዳርቻ ያላት ኤርትራ፣ ወደብ አልባ የሆነችውን ኢትዮጵያን ግዛት በማስፋፋት ምኞት ትከስሳታለች።
በሚያስደንቅ ሁኔታ አሥመራ አሁን ወዳጅነቷን ከትግራይ መሪዎች ጋር በማድረጓ ዳግም ግጭት የሚቀሰቀስ ከሆነ ቀደም ሲል ከነበረው በተቃራኒ ኤርትራ ለትግራይ ኃይሎች የምትወግን ይመስላል።

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
አዲስ አበባም ከኢትዮጵያ እና ከኤርትራ ጋር በምትዋሰነው ሱዳን ውስጥ በሚካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ተሳትፎ እንዳላት ትከሰሳለች።
ምንም እንኳን ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ብታስተባብልም በርካታ ሪፖርቶች አዲስ አበባ የሱዳን ተፋላሚ አንጃ የሆነውን ፈጥኖ ደራሽ ኃይልን (አርኤስኤፍ) እንደምትደግፍ ያመለክታሉ።
የኤርትራ እና የትግራይ ኃይሎችም ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ጋር እየተፋለመ ከሚገኘው ከሱዳን ጦር ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸው ለረጅም ጊዜ ሲነገር ቆይቷል።
ይህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሰላም ፈጣሪነትን ሚና ሊጫወቱበት የማይችሉትን እና በቀጣናው ውስጥ ሊሠራጭ የሚችል አደገኛ ሁኔታን ይፈጥራል።
በዐቢይ መንግሥት እና በትግራይ ክልል ውስጥ የበላይ በሆነው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መካከል የነበረው ጠላትነት በጥቅምት 2015 ዓ.ም. በተፈረመው የሰላም ስምምነት ይቋጫል ተብሎ ነበር።
ነገር ግን ሁለቱም ወገኖች ያንን ስምምነት በመጣስ እርስ በእርሳቸው ይካሰሳሉ።
በትግራይ የተካሄደው ጦርነት ባለንበት ክፍለ ዘመን እጅግ አደገኛ ከሆኑት መካከል አንዱ ሲሆን፣ የአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይ ጦርነቱ ክልሉን ወደ ረሃብ እያመራ በነበረበት ወቅት ወደ 600 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች እንደሞቱበት ገምቷል። በወቅቱ መንግሥት ውድቅ ቢያደርገውም ለክልሉ የሚቀርበውን የምግብ እርዳታ በማገድ ተከስሶ ነበር።
የተደቀኑት "አደጋዎቹ ተጨባጭ እና በሁለቱም ወገኖች የሚመሩ ናቸው" ሲሉ በአንድ ወቅት ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ ይሠሩ የነበሩት የአፍሪካ ጉዳዮች ተንታኝ ካሜሮን ሁድሰን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከምርጫው በፊት ህወሓት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የተሾመውን የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር አፍርሶ ከጦርነቱ በፊት የነበረውን አስተዳደር ወደ ነበረበት መልሷል።
"[ህወሓቶች] እየጨመረ ላለው ውጥረት ተጠያቂ ናቸው፤ ለጦርነት ዳግም ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን የሚጠቁሙ እንቅስቃሴዎችን እና መግለጫዎችን ሲሰጡ ቆይተዋል" ሲሉ ሃድሰን ይናገራሉ።
ህወሓት ወጣቶችን በግዳጅ ወደ ሠራዊቱ እንዲቀላቀሉ እያስገደደ መሆኑን የሚያመለክቱ ዘገባዎች እየወጡ ነው።
በትግራይ የሚንቀሳቀሰው ተቃዋሚው የሳልሳይ ወያኔ የፖለቲካ ፓርቲ አባል የሆኑት ሸዊት ውዳሴ ለቢቢሲ እንደተናገሩት "በርካታ ወጣቶች ለውትድርና እየተመለመሉ በመሆኑ የትግራይ ሕዝብ ስጋት ውስጥ ነው።"

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
በአድዋ ከተማ የሚኖር አንድ ወጣት ለቢቢሲ ትግርኛ እንደተናገረው ሲቪል የለበሱ የታጠቁ ሰዎች ወደ ቤቱ እንደሄዱ እና "በትጥቅ ትግሉ ውስጥ እንድንሳተፍ እንደያዙን ነግረውናል" ብሏል።
የክልሉ ባለሥልጣናት ግን "በግዳጅ የሚደረግ ምልመላ" እንደሌለ አስተባብለዋል።
"ወጣቶቹ እራሳቸውን ለመከላከል ሥልጠና እየወሰዱ ነው" ሲሉ የሰሜን ምዕራብ ትግራይ የደኅንነት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ አባዲ ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ሃድሰን እንደሚሉት፣ እነዚህ የህወሓት ድርጊቶች የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "ከስምምነቱ ወጥቶ በትግራይ ስጋትን የሚፈጥር እርምጃዎችን በመውሰዱ ነው።"
የአውሮፓ ኅብረት በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ውጥረት "በአፋጣኝ እንዲረግብ" በቅርቡ ባወጣው ማስጠንቀቂያ ጠይቆ ነበር።
በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል ከአራት ዓመት በፊት ለተደረሰው የሰላም ስምምነት ዋና አሸማጋይ የነበረችው አሜሪካ ባለፈው ሳምንት "አክራሪ የህወሓት አባላት እና የቅርብ ቤተሰቦቻቸውን" ዒላማ ያደረገ የቪዛ ዕገዳ ጥላለች።
ዕገዳው እነማንን እንደሚመለከት በስም ባይጠቀስም "በትግራይ ክልል የተፈጠረውን ቀውስ ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት የሚያደናቅፉ ወይም ተባባሪዎቻቸውን" የሚመለከት ነው ብሏል።
በዓለም አቀፍ የክራይሲስ ግሩፕ የባለሙያዎች ቡድን የአፍሪካ ቀንድ ተንታኝ የሆኑት ማግነስ ቴይለር፣ በፍጥነት ወደ ጦርነት ይገባል ብለው አያምኑም። ነገር ግን እየቀጠለ ያለው ዝቅተኛ ውጥረት "አደገኛ ሁኔታ" ነው ብለዋል።
"አዲስ አበባ ህወሓት ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር እየወገነ ነው ብላ በምታምንበት በዚህ በጣም በተካረረ እና መርዛማ ቀጣናዊ ፖለቲካ ውስጥ ትግራይን ማዕከል ያደረገ አካባቢያዊ ግጭት የመፍጠር ዕድሉ ሰፊ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የትግራይ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ለሆነው ለሸዊት ችግሩ የሁለቱም ወገኖች ግትር መሆን እና "ልዩነቶቻቸውን በድርድር ለመፍታት" ፈቃደኛ አለመሆናቸው ነው።
"የበላይነታቸውን ለማረጋገጥ ትክክለኛውን ጊዜ እየጠበቁ እንደሆነ አምናለሁ። ይህ ደግሞ ወደ ውጊያ ሊያመራ ይችላል።"
እንደ ሃድሰን ገለጻ ደግሞ፣ የሚቀጥሉት ወራት የኢትዮጵያን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚወስኑ ሊሆኑ ይችላሉ።
"ብዙዎቻችን ዐቢይ የፖለቲካ ሥልጣኑን ማጠናከር ለትግራይ እና ለግጭቱ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያበቃ ለማድረግ ወይም መፍትሄ ለመስጠት እንደሚጠቀምበት መስጋታችን ተገቢ ይመስለኛል።"















