ፌስቡክ መጠሪያውን 'ሜታ' በሚል ስያሜ ቀየረ

አዲሱ ስምና መለያ

የፎቶው ባለመብት, Meta

ታትሟል

ግዙፉ ማኅበራዊ ሚዲያ ፌስቡክ ስሙን ወደ ሜታ መቀየሩን ይፋ አደረገ።

ድርጅቱ ከማኅበራዊ ሚዲያ ጎን ለጎን ወደ ቨርችዋል ሪያሊቲ እና ሌሎችም የቴክኖሎጂ ዘርፎች እየገባ መሆኑንም አያይዞ ገልጿል።

የፌስቡክ የስም ለውጥ በድርጅቱ ያለውን ለውጥ የሚያሳይ እንደሆነ ተጠሙሟል።

የስም ለውጡ የተደረገው በድርጀቱ ላይ ነው እንጂ በሚሰጣቸው የፌስቡክ፣ የኢንስታግራም እና የዋትስአፕ አገልግሎቶች ላይ ለውጥ አልተደረገም።

የቀድሞው የፌስቡክ ሠራተኛ ሚስጥራዊ ሰነዶችን ማጋለጧን ተከትሎ የፌስቡክ ስም እየተብጠለጠ ይገኛል።

የስም ለውጡ የተደረገው ፈስቡክ እየደረሰበት ያለውን ወቀሳ ተከትሎም ነው።

ፍራንሲስ ሀውገን የተባለችው የፌስቡክ የቀድሞ ተቀጣሪ "ድርጅቱ ከተጠቃሚዎቹ ይልቅ ትርፍን ያስቀድማል" ስትል በማስረጃ አስደግፋ ፌስቡክ ኮንናለች።

ኢትዮጵያ ጨምሮ በሌሎችም አገሮች የጥላቻ ንግግር፣ ሐሰተኛ መረጃ እና ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶችን ፌስቡክ እንዳላስቆመ መግለጿም አይዘነጋም።

ከአሜሪካ እንዲሁም በእንግሊዘኛ ከሚጻፉ ውጪ ያሉ የጥላቻ ንግግሮችን ማስቆም ባለመቻሉ ፌስቡክ ተወቅሷል።

ኢንስታግራም የታዳጊዎችን የአእምሮ ጤና እያቃወሰ መሆኑም ሾልከው ከወጡ ሰነዶች ተገኝቷል።

ፌስቡክ በበኩሉ ሾልከው የወጡት ሰነዶች ትክክለኛውን የፌስቡክ ገጽታ አያሳዩም ሲል አጣጥሏል።

የፌስቡክ መሪ ማርክ ዙከርበርግ አዲሱን የድርጅቱን ስም ሲያስተዋውቅ 'ሜታቨርስ' የተባለ አሠራር ሊጀምሩ እንደሆነም ይፋ አድርጓል።

ሜታቨርስ ሰዎች በቨርችዋል ሪያሊቲ (ከገሀዱ ዓለም ጋር በሚቀራረብ የዲጂታል ዓለም) ውስጥ ሆነው እንዲሠሩ፣ ከሰዎች ጋር እንዲነጋገሩ እና ጌም እንዲጫወቱም ያስችላቸዋል።

ፌስቡክ አሁን ያለው ስም ይህንን አሠራር እንዲሁም ለወደፊት ያቀዳቸውን ፕሮጀክቶች ስለማይገልጽ የስም ለውጥ እንዳስፈለገ ማርክ ተናግሯል።

"በጊዜ ሂደት ሰዎች ሜታቨርስ ድርጅት መሆናችንን ይገነዘባሉ ብዬ አምናለሁ። አሁን ያሉንን ማኅበራዊ ሚዲያዎች ለወደፊት ከምንጀምራቸው ፕሮጀክቶች ጋር የሚገልጽ አዲስ ስም መያዝ አለብን" ብሏል።

ፌስቡክ ከዚህ ቀደም የሚታወቅበትን የአውራ ጣት (ላይክ የሚያሳይ ጣት) ምስልም ቀይሯል። ካሊፎርኒያ በሚገኘው በፌስቡክ ዋና መሥሪያ ቤት አዲሱ የድርጅቱ ምስል የኢንፊኒቲ (አለማለቅን የሚያሳይ ምልክት) ሆኗል።

ሜታ የሚለው ቃል የግሪክ ትርጉሙ 'በላይ' ነው።

ቨርችዋል ሪያሊቲ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ገናና ስም ካላቸው አንዱ ነው። የወደፊቱ ዓለም ማሳያ እንደሆነም ይነገራል።

በዲጂታል ዓለም የሚፈጠረው ቨርችዋል ሪያሊቲ ድምጽን፣ ምስልን እና ሌሎችም ስሜቶችን የእውነት የተፈጠሩ ያህል አጉልቶ ያሳያል፣ ያስደምጣልም።

በወደፊቱ ዓለም ሰዎች ሥራ የሚሠሩት፣ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚጠያየቁት ወይም የሙዚቃ ኮንሰርት የሚታደሙትም በቨርችዋል ሪያሊቲ (ቪአር) ይሆናል ተብሎ ይታመናል።

ፌስቡክ ይህንን የቨርችዋል ሪያሊቲ አገልግሎት አካትታለሁ ብሎ ስሙን ወደ ሜታ ቢቀይርም፤ የስም ለውጡን ያደረገው የጠለሸ ገጽታውን ለማጥራት ነው የሚል አስተያየት ተሰንዝሯል።

ፌስቡክ የሚለው ስም ከብዙ ትችቶች እና ወቀሳዎች ጋር ተያይዞ እየተነሳ ስለሆነ ስሙን በመለወጥ ገጽታውን ለማሻሻል እየሞከረ ሊሆን ይችላል።

በሌላ በኩል ሜታቨርስ የተባለው አሠራር ገና ያልተጀመረ እና ለመጀመርም ጊዜ የሚወስድ እንደመሆኑ፤ ባልተጀመረ አገልግሎት አስታኮ የፌስቡክን ስም ወደ ሜታ መቀየር ትርጉም አይሰጥም የሚሉም አሉ።

ሜታ የሚለው አዲሱ የፌስቡክ ስም እምብዛም ታዋቂ ላይሆን ይችላል ብለው አስተያየት የሰጡ አልጠፉም። እንደ ምክንያት ያስቀመጡት ደግሞ ከዚህ ቀደም ግዙፍ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች ስማቸውን ቢቀይሩም አዲሱ ስም ታዋቂ አለመሆኑን ነው።

ለምሳሌ እአአ በ2015 ጉግል የአጋር ድርጅቱን ስም ወደ አልፋቤት ቢቀይርም ስሙ ብዙም እውቅና አላገኘም።