የኒውካስትል ቡድን በሳዑዲ አረቢያዊ መግዛቱን አወዛጋቢ ያደረጉት ስድስት ምክንያቶች

የጀማል ኻሾግጂን በሳዑዲ አረቢያ ባለስልጣናት መገደል የሚቃወም ማስታወቂያ የያዘ መኪና በኒውካስል ዩናይትድን ስታዲም ሴንት ጄምስ ፓርክ አቅራቢያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የጀማል ኻሾግጂን በሳዑዲ አረቢያ ባለስልጣናት መገደል የሚቃወም ማስታወቂያ የያዘ መኪና በኒውካስል ዩናይትድን ስታዲም ሴንት ጄምስ ፓርክ አቅራቢያ
ታትሟል

በሳዑዲ አረቢያ በሚመራው ጥምረት የእንግሊዙን ኒውካስትል ዩናይትድ የእግር ኳስ ክለብ መግዛቱ በብዙ ደጋፊዎች ዘንድ ተቀባይነት ቢያገኝም በባሕረ ሰላጤዋ ንጉሣዊ ግዛት ውስጥ ባለው የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ምክንያት ትችት ገጥሞታል።

አወዛጋቢ ከሆኑበት ምክንያቶች አንዳንዶቹን እነሆ፡

አሳፋሪው ግድያ

የሳዑዲ አረቢያን መንግሥት ተቺ የነበረው እና ጥቅምት 2018 የተገደለው የጋዜጠኛው ጀማል ኻሾግጂ ጉዳይ የአገሪቱን ስም በመላው ዓለም አጉድፎታል።

በተመድ የተሾመው የሰብዓዊ መብት ኤክስፐርት እንዳለው ኻሾግጂ ኢስታንቡል በሚገኘው የሳዑዲ ቆንስላ ቅጥር ግቢ ውስጥ በአገሪቱ ወኪሎች ቡድን "በጭካኔ ተገድሏል" ብሏል።

የሳዑዲ አረቢያ ገዥ አልጋ ወራሽ ልዑል መሐመድ ቢን ሰልማን እና ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናትም ተከሰዋል። ምንም እንኳን ልዑሉ ምንም ዓይነት ተሳትፎ እንደሌላቸው ቢያስተባብሉም በውጭ አገር የነበራቸው ስም ክፉኛ ተበላሽቷል።

የኻሾግጂ እጮኛ ሃቲስ ሴንጊዝ ሳዑዲ አረቢያ የኒውካስትል ቡድንን መግዛት "ልብን የሚሰብር" ስትል ገልጻዋለች።

በኒውካስል 80 በመቶ ድርሻ ያለው መንግሥት ስር የሚተዳደረው የዘውዱ ኢንቨስትመንት ፈንድ በመሐመድ ቢን ሳልማን ይመራል። ፕሪሚዬር ሊጉ ግን የሳዑዲ መንግሥት ክለቡን እንደማይቆጣጠር ማረጋገጫ አግኝቻለሁ ብሏል።

የሴቶች መብት ተከራካሪዋ ሉጂያን አል ሃቱሉ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የሴቶች መብት ተከራካሪዋ ሉጂያን አል ሃቱሉ ከሦስት ዓመት እስር በኋላ ተለቃለች

የሴቶች መብት ተሟጋቾች እስራት

እአአ በ2018 የሳዑዲ ባለሥልጣናት በሴቶች ላይ የተጣለውን መኪና የማሽከርከር እገዳን ለማንሳት የነበረውን ዘመቻ የመሩ 13 የመብት ተሟጋቾችን በቁጥጥር ስር አዋሉ።

ከሴቶቹ ቢያንስ አራቱ በመርማሪዎች ከመሰቃየታቸው በተጨማሪ ወሲባዊ ትንኮሳ ደርሶባቸዋል ተብሏል።

እአአ በ2020 ፍርድ ቤት ታዋቂዋን አክቲቪስት ሉጃይን አል-ሃትሎልን በመንግሥት ላይ ወንጀል በመሥራት ጥፋተኛ ተብላለች። እሷ ግን ክሱን አስተባብላለች። የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎችም የቀረበባት ክስም "ሐሰተኛ" እንደሆነ ገልጸዋል።

ፍርድ ቤት በካቲት ወር ከእስር ለመልቀቅ መንገዱን የከፈተላትን የአምስት ዓመት የእስር ቅጣቷን በከፊል ቢያግድም የጉዞ እና ሌሎች እገዳዎች ተጥሎባታል።

ከአንዷ በስተቀር ሌሎቹ አክቲቪስቶች ሁሉም በዋስ ከእስር ወጥተዋል ወይም የታገዱ ቅጣቶችን እየፈጸሙ ነው ተብሏል።

አሪጃ ባለሥልጣናትን ተችቶ ትዊተር ላይ በመጻፉ ስቃይ ተፈጽሞበት የ20 ዓመት እስር ከተፈረደበት ወንድሟ አብዱል ራህማን ጋር

የፎቶው ባለመብት, Areej Al-Sadhan

የምስሉ መግለጫ, አሪጃ ባለሥልጣናትን ተችቶ ትዊተር ላይ በመጻፉ ስቃይ ተፈጽሞበት የ20 ዓመት እስር ከተፈረደበት ወንድሟ አብዱል ራህማን ጋር

ተቃዋሚዎችን ማፈን

የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሠራተኛ ማኅበራት እና ገለልተኛ የሰብዓዊ መብት ቡድኖች በተከለከሉባት በሳዑዲ አረቢያ ተቺዎችን ለመቆጣጠር የተወሰደው እርምጃ የሴቶች መብት ተሟጋቾች ላይ ብቻ አያበቃም።

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች እንደሚሉት በደርዘን የሚቆጠሩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ ምሁራን፣ የሐይማኖት አባቶች እና የለውጥ አራማጆችም እአአ ከ2017 ጀምሮ ለእስር ተዳርገዋል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንዳለው ከሆነ ብዙዎቹ ፍትሃዊ ያልሆነ የሽብርተኝነት እና የሳይበር ወንጀል ክስ ገጥሟቸዋል። የሞት ቅጣትን ጨምሮ ከባድ ቅጣትም ተጥሎባቸዋል።

ኒውካስል ከመግዛታቸው ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ባለሥልጣናትን በመተቸት የጻፈውን ሳዑዲ-አሜሪካዊውን የእርዳታ ሠራተኛ አብዱል ራህማን አል-ሳዳንን የ20 ዓመት እስራቱን ፍርድ ቤት አጽንቶበታል።

እህቱ እንዳለችው ከመከሰሱ በፊት "በአሰቃቂ ሁኔታ ስቃይ ደርሶበታል" ኒውካስልን መግዛታቸው የሳዑዲ አረቢያ በደሎችን "ለማጠብ" የተደረገ ሙከራ ነውም ብላለች።

የፈራረሰ ህንጻ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ከባድ ሰብአዊ ቀውስን ያስከተለው የየመን ጦርነት

መን ጦርነት

ጎረቤት የመን የሰብዓዊ ጥፋት ባስከተለው ወታደራዊ ዘመቻ ሳዑዲ አረቢያ በከፍተኛ ሁኔታ ተወቅሳለች።

የየመን አማጽያን አብዛኛውን የምዕራባዊውን የአገሪቱ ክፍል ተቆጣጥረው ፕሬዚዳንቱ ወደ ውጭ አገር እንዲሰደዱ ካደረጉ በኋላ በሳዑዲ የሚመራው ጥምረት እአአ በ2015 ጣልቃ ገባ።

በውጊያው ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል። ጉዳዩን የሚከታተል አንድ ቡድን 8,700 ሲቪሎች በሕብረቱ ጦር የአየር ጥቃቶች ምክንያት ለሞት መዳረጋቸውን አስታውቋል።

በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ደግሞ እንደ ምግብ እጥረት፣ የጤና አገልግሎቶች እና የመሠረተ ልማት አውታሮች ባሉ በተዘዋዋሪ ምክንያቶች እንደሞቱ ይገመታል።

የሕብረቱ ከፊል እገዳ ሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸውን 20 ሚሊዮን ሰዎች ለመርዳት በሚደረገው ጥረት ላይም እንቅፋት ሆኗል።

የተባበሩት መንግሥታት ባለሙያዎች በግጭቱ የተሳተፉ ሁለቱም ወገኖች የጦር ወንጀሎችን ፈጽመው ሊሆን ይችላል ቢልም ሕብረቱ የጦርነት ሕጎችን አክብሬያለሁ ይላል።

የሳዑዲን የሞት ቅጣትን በመቃወም አሜሪካ ውስጥ የተደረገ ሰልፍ ተሳታፊ

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency

የምስሉ መግለጫ, ሳዑዲ አረቢያ በርካታ የሞት ፍርድ ከሚፈጸምባቸው አገራት መካከል አንዷ ናት

የሞት ፍርድ

ሳዑዲ አረቢያ ከዓለም ከፍተኛ የሞት ፍርድ ፈጻሚ አገራት መካከል ናት።

በአምነስቲ ኢንተርናሽናል መሠረት ከሆነ ከጥር እስከ ሐምሌ 2021 ባለው ጊዜ ውስጥ ቢያንስ 40 ሰዎች ተገድለዋል።

በወጣት ወንጀለኞች ላይ የሞት ቅጣትን እንደሰረዘ ቀደም ሲል መንግሥት ዋስትና ቢሰጥም ባለፈው ሰኔ አንድ ሰው 17 ዓመት እያለ ፈጽሞታል በተባለው ወንጀል ምክንያት ተገድሏል።

ሙስጠፋ አል-ዳርዊሽ የእምነት ቃሉን የሰጠው በደረሰበት ስቃይ መሆኑን በችሎት ላይ ቢገልጽም በፍርድ ፀረ-መንግሥት ተቃውሞዎች ተሳትፈሃል በሚል እና በሌሎች በርካታ ክሶች ተፈርዶበታል።

የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን በተመለከተ

ሳዑዲ አረቢያ የጾታዊ ግንኑነት ዝንባሌን ወይም የጾታ ማንነትን የሚመለከት ሕግ ባይኖራትም ዝሙት እና "ሥነ ምግባር የጎደለው" የምትለውን የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን እንዲሁም ከጋብቻ ውጪ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎችን ትቀጣለች።

የፀረ-ሳይበር ወንጀል ሕግም በድረ ገጽ "የሕዝብን ሥርዓት፣ ሐይማኖታዊ ሥነ ምግባርን እና ግላዊነትን" የሚቃረን እንቅስቃሴም በወንጀል ያስቀጣል።

የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን ጨምሮ እኩል መብቶች እንዲከበሩ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የጠየቀውን የየመን ጦማሪን በሐምሌ 2020 ላይ ፍርድ ቤት የ10 ወር እስራት እና ከአገር እንዲባረር ፈረዶበታል።