የደቡብ ሱዳን አመራሮች በሕገወጥ ገንዘብ ዝውውር ተዘፍቀዋል-ተመድ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በደቡብ ሱዳን ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊ እና የንግዱን ዘርፍ እየመሩ ያሉ ግለሰቦች በሕገወጥ መንገድ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር በማዘዋወር በአገሪቱ ውስጥ ውስጥ ባለው አለመረጋጋት ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ነው በማለት የተባበሩት መንግሥታት የባለሙያዎች ቡድን ከሰሰ።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እንዳስታወቀው በደቡብ ሱዳን ከአውሮፓውያኑ 2018 ጀምሮ "የመንግሥት ባለስልጣናትና ከእነሱ ጋር ግንኙነት ያላቸው አካላት ቢያንስ በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር በሕገወጥ መንገድ አዘዋውረዋል እንዲሁም አጭበርብረዋል" ብሏል።
ይህ ግን በአገሪቱ ውስጥ እየተፈፀመ ያለውን ሕገወጥ ገንዘብ ዝውውር ደረጃን አያሳይም ተብሏል። በአገሪቱ ውስጥ የተንሰራፋው ሙስና ያለውን የሰብዓዊ መብትና የፀጥታ ሁኔታን ያዳክማል ብሏል ሪፖርቱ።
ከአውሮፓውያኑ 2018 ጀምሮ 73 ሚሊዮን ዶላር በሕገወጥ መንገድ ተዘዋውሯል። ኮሚሽኑ ይህ አሃዝ ከተዘረፈው አጠቃላይ የገንዘብ መጠን ባጣም ጥቂቱ ነው ብሏል።
"የብዝበዛውንና ዘረፋውን ሁኔታ በምናይበት ወቅት ፖለቲከኞች፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ዓለም አቀፍ ኮርፖሬሽኖች፣ ወታደራዊ አመራሮች እና ዓለም አቀፍ ባንኮች መሳተፋቸውን በግኝታችን ማረጋገጥ ችለናል" በማለት የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር ያሲሚን ሱካ ሪፖርቱን በሚያቀርቡበት ወቅት አስረድተዋል።
ሪፖርቱ በተጨማሪም የደቡብ ሱዳን የነዳጅ ኢንዱስሪ "ተጠያቂነት በሌለው የነዳጅ ጥምረት ቡድን" በበላይነት የሚመራ ሲሆን በዚህም አካቢውን መበከል ጨምሮ ለማኅበረሰቡ ጤና ጠንቅ ሆኗል ብሏል።
እንዲህ አይነት ብዝበዛዎችና ዘረፋዎች እየተፈፀሙባት ያለችው ደቡብ ሱዳን ሁለት ሦስተኛ ወይም 7.2 ሚሊዮን የሚሆነው ሕዝቧ ምግብ ለማግኘት በየቀኑ እየታገለ ይገኛል።
የባለሙያዎቹን ሪፖርት በተመለከተ የደቡብ ሱዳን መንግሥት የሰጠው ምላሽ የለም።












