የኢትዮጵያ ኤምባሲና ቆንስላዎችን ለመዝጋት መወሰን የሚኖረው አንድምታ

የፎቶው ባለመብት, Ministry of Foreign Affairs/FB
ባለፈው ረቡዕ ኢትዮጵያ በአልጄሪያ ዋና ከተማዋ አልጀርስ የሚገኘው ኤምባሲዋን ለመዝጋት እንወደሰነችና ከአገሪቱ ጋር የሚኖራትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ግን እንደሚቀጥል ኤምባሲው አስታውቋል።
በተጨማሪም ኢምባሲው የሚዘጋው እየተካሄደ ባለው ማሻሻያና ከኮቪድ-19 ጋር በተገናኘ እንደሆነም ገልጿል።
በአልጀርስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ ካሏት ኢምባሲዎችና ቆንስላዎች መካከል ግማሽ ያህሉን እንደምትዘጋ ካሳወቁ በኋላ በይፋ መዘጋቱ የታወቀ የመጀመሪያው ኤምባሲ ነው።
በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ "አሁን በየቦታው ዶላር ከምንበትን ለስድስት ወር ወይም ለአንድ ዓመት ካሉን ኤምባሲዎች ቢያንስ 30ዎቹ መዘጋት አለባቸው። እነዚህ ተዘግተው አምባሳደራቸው እዚህ ሆኖ ይሰራል" በማለት ኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች ሊዘጉ እንደሚችሉ ጠቁመው ነበር።
ከሰባት ዓመት በፊት ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተቀላቀሉት እና አልጄሪያ በነበረው ኤምባሲ ለሦስት ዓመታት ያገለገሉት የዲፕሎማሲ ባለሙያው ሰመረ ኪዳነ ውሳኔው ድንገተኛና አስደንጋጭ ነው ይላሉ።
ይህ ውሳኔ ከመምጣቱ ከአራት ወር በፊት ሥራቸውን መልቀቃቸውን ገልፀው፣ "ይህንን ስሰማ ግን ደንግጫለሁ፤ አልጠበቅኩትም። ብዙ የሰራሁበት ኤምባሲ ስለሆነ እና ጉዳቱም ከፍተኛ ስለሆነ ውሳኔው ከብዶኛል" ሲሉ የተፈጠረባቸውን ስሜት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፈው ወር ለሁሉም ሚስዮኖች በጻፈው ደብዳቤ 'ሠራተኞች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ስለተወሰነ በተመደቡበት ቦታ ሲገለገሉበት የነበረውን ንብረት አስረክበው እስከ ነሐሴ 15፣ 2013 ዓ.ም ባለው ጊዜ ወደ ዋና መሥሪያ ቤት [አዲስ አበባ] ሪፖርት እንዲያደርጉ' አሳስቧል።
ሆኖም የተለያዩ የኤምባሲና የቆንስላ ጽህፈት ቤቶች ይሰሩ የነበሩ ሠራተኞች በኤምባሲዎች መዘጋትና በድንገተኛው ጥሪ ምክንያት ሥራቸውን አቁመው ወደ አገራቸው እንደማይመለሱ እየተነገረ ነው።
ከእነዚህም መካከል በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ዲፕሎማት በመሆን ላለፉት ሁለት ዓመታት በብራሰልስ የአውሮፓ ሕብረት ጉዳዮችን ሲከታተሉ የቆዩት መርከብ ነጋሽ አንዱ ናቸው።
አቶ መርከብ ሲሰሩበት የነበረው በብራሰልስ የሚገኘው ኤምባሲ ሠራተኞች በአጠቃላይ ወደ አገር ቤት ተመልሰው ሪፖርት እንዲያደርጉ ደብዳቤ ደርሷቸዋል።
በዚህም መሰረት አብዛኛው ዲፕሎማት ተመልሶ ስልጠና ተሰጥቶት እንደ አስፈላጊነቱ እንደገና ሊመደብም ላይመደብም ይችላል የሚል ማብራሪያ እንደተሰጣቸው የሚናገሩት አቶ መርከብ፣ "ይህ አሳማኝ አይደለም" ይላሉ።
በዚህ ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ እንደማይመለሱና ሥራ እንዳቆሙ ተናግረዋል።
ነገር ግን በመንግሥት እንዲዘጉ ከተወሰኑ ኤምባሲዎችና ቆንስላዎች መካከል የብራሰልሱ ኤምባሲ እንደማይገኝበት ቢቢሲ አረጋግጧል።
አቶ መርከብ "ሪፖርት አላደረግኩም፤ ግን እዚህ የነበረኝን ኃላፊነት እና እቃ አስረክቤያለሁ። አልመለስም" በማለት ለዚህ መነሻ ሆኖኛል የሚሏቸውን ምክንያቶች ያስቀምጣሉ።
በትግራይ ክልል ያለው ጦርነት አንዱ ነው የሚሉት አቶ መርከብ፣ በክልሉ የተፈጠረው ቀውስ በቀጥታ ጫና እንደሚያደርስበት በመግለጽ "አገሪቷ ላይ ያለው ሁኔታ ስለሚታወቅ ከአሁን በኋላ ለዚህች አገር ለማገልገል ፍላጎት የለኝም" ብለዋል።
ባለፉት ወራት እስከ 'መሰወር' የሚደርስ እስራትና እንግልት በትግራይ ተወላጆች ላይ እየደረሰ ነው የሚለውን የአለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጓቾች ሪፖርቶች በመጥቀስም "ለራሴና ለቤተሰቦቼ ደኅንነት ስለሚያሰጋኝ ላለመመለስ ወስኛለሁ" ሲሉ ተናግረዋል።
መንግሥት ግን ለዚህ ውንጀላ ምላሽ ሲሰጥ 'ማንም በማንነቱ ምክንያት' እንዳልታሰረ በመግለጽ፤ መንግሥት አሸባሪ ብሎ ከፈረጀው ከህወሓት ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎችን ተጠያቂ የማድረግ ሥራዎች እንደሆኑ መግለጹ ይታወሳል።
እስከ ባለፈው የሐምሌ ወር ለዘጠኝ ዓመታት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጂቡቲና አቡዳቢ በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች የተለያዩ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን ሲሰራ የቆየው ዳዊት ንጉሤ በበኩሉ ውሳኔውና እየቀረቡ ያሉ ምክንያቶች አጥጋቢ አይደሉም ይላል።
በዚህም የተነሳ "ጥቂት የማይባሉ ባሉበት አገር ወይም ወደ ሌላ አገር በመሄድ የመቅረት አዝማሚያ" እንዳላቸውም ተናግሯል።
"እኔ የማውቃቸው የሥራ ባልደረቦቼ ደንግጠዋል፤ አንዳንዶቹ ደግሞ የመመለስ ፍላጎት የላቸውም። የጠራ ነገር ስለሌለ ወደ አገር ቤት ተመልሰንም ሥራ ላይ መቀጠል ላይኖር ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።" ብሏል።
እነዚህ ወደ አገራቸው አንመለስም የሚሉ የሚስዮኖቹ ልዑካን ከዚህ በፊት በፖለቲካዊ ውሳኔ የተመደቡና ልምድ የሌላቸው እንደሆኑ የሚተቹ ወገኖች አሉ።
ወደ አገራቸው እንደማይመለሱ ለቢቢሲ የተናገሩት ሁለቱ ግለሰቦች ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው በቀጥታ ወደ ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ በመቀላቀል በተለያዩ የወደብ፣ ሕዝብ ለሕዝብ፣ የኢንቨስትመንትና ሌሎች የዲፕሎማሲ ሥራዎች የሰለጠኑና ሲሰሩበት የነበረ መሆናቸውን ይናገራሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ ላይ ኤምባሲዎች ብዙ ገንዘብ እንደሚወጣባቸው በመግለጽ ሚንስቴሩን፣ እንደ አዲስ በማጠናከር ብዙ አዲስ ወጣቶች ሰልጥነው ወደ መሥሪያ ቤቱ እንደተቀላቀሉ ተናግረዋል።
ከዚህ ውጪ "ከኤምባሲዎች በማይተናነስ መልኩ ከአምባሳደር በላይ የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን አሉ። ውጪ ያላችሁ ኢትዮጵያውያንም ለዚህ ተዘጋጁ፤ ኢትዮጵያ ከዚህ በላይ አትችልም" የሚል መልዕክት አስተላልፈው ነበር።
የኤምባሲዎች መዘጋት ምክንያት ምንድን ነው?
ከቀናት በፊት መዘጋቱን ያሳወቀው በአልጄሪያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ላይ እንዳስታወቀው ለመዘጋቱ ምክንያት የሆነው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ያስከተለው አሉታዊ ጫና፣ የገንዘብ እጥረትና የምጣኔ ሀብት ቀውስ ነው ይላል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ ማሻሻያዎችን በማካሄድ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው ዓለም የበለጠ የምትወከልበትን መንገድ እንደገና ማደራጀት አስፈላጊ መሆኑ በመታመኑ እንደሆነ ኤምባሲው አስታውቋል።
መንግሥት በአገሪቷ ካለው ለውጥ ጋር በተያያዘ መንግሥት በመሥሪያ ቤቱ የተሻሻለ የሲቪል ሰርቪስ ሥርዓት ለመዘርጋት የሁሉም ተቋማት አደረጃጀትና አሰራር እየተፈሸ መሆኑን በመጥቀስ ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ላይ ለውጥ ለማምጣት እየተሰራ መሆኑን አመልክቷል።
በዋናነት ግን በዓለም ደረጃ ያጋጠሙ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ግምት ውስጥ በማስገባት ማሻሻያ ለማድረግ መወሰኑንም ምንጮቻችን ገልጸዋል።
ገንዘብ የለም ስለተባለ ብዙ ኤምባሲና ቆንስላ ጽህፈት ቤት አያስፈልግም በሚል የሚዘጉ፣ በአንድ አምባሳደር እንዲሰሩ የተደረጉ፣ ከአዲስ አበባ ይሸፈናሉ የተባሉና አንዳንዶቹም የሰው ኃይላቸው ተቀይሮ አልያም ተቀንሶ እንዲሰሩ የሚደረጉ እንዳሉ ተነግሯል።
እስከ አሁን ግን ይህንን በተመለከተ የተሰጠ ዝርዝር ይፋዊ መረጃ የለም።
ቢቢሲ ግን በሙስካት፣ ዘ-ሄግ፣ ደብሊን፣ ሎስ አንጀለስ፣ ሚኒሶታ፣ ፍራንክፈርት፣ ኢስታንቡል፣ ጓንጁ፣ ሻንጋይ፣ ቾንቺን፣ ሙምባይ፣ አቢጃን፣ ኩዌት፣ ጃካርታ፣ ካምቤራ፣ ብራዚሊያ፣ ኦታዋ፣ ሃቫና፣ ሐራሬ፣ ራባት፣ አልጀርስ፣ ካይሮ፣ ዳካር፣ አክራ፣ ኪጋሊ፣ ኪንሻሳ፣ ሴዑል፣ ዶሃ፣ ባህሬን፣ ስቶክሆልም የሚገኙ ሚስዮኖች እስከ ጥቅምት ወር ባለው ጊዜ እንደሚዘጉ ከምንጮቹ ካገኘው ሰነድ ላይ ተመልክቷል።
እነዚህ ሚሲዮኖች ሲገለገሉባቸው የነበሩ እቃዎች ወደ አገር ቤት እንዲመለሱና ባሉበት እንዲታቀቡ ሲል፤ በአንዳንዶቹ ሚሲዮኖች የነበሩ እቃዎች ግን ረጅም ዓመታት ያገለገሉ ስለሆኑ የፌደራል መንግሥት ንብረት ማስወገድ መመሪያና የአገራቱን ሕግ በመከተል እንዲወገዱ አሳስቧል።
ከዚህ በተጨማሪ ቢቢሲ ያገኘው ሰነድ፤ በኪጋሊ እና ታንዛኒያ ዶዶማ የነበሩ ኤምባሲዎች በ'ላፕቶፕ አምባሳደር' እና ከዋና መስሪያ ቤት [አዲስ አበባ] ሆኖው እንዲሰሩ መወሰኑን በመግለጽ ለሁሉም ሠራተኞች ስልጠና መዘጋጀቱን ያስረዳል።
የትግራይ ጦርነት እና የኤምባሲዎች መዘጋት
ጦርነቱ ብዙ ኪሳራ አድርሷል የሚሉት ሰመረ "የሁሉም ጦርነት ኪሳራ ብዙ ስለሆነ ያጋጠመው ኢኮኖሚያዊ ችግርም ከዚህ የሚመነጭ ይመስለኛል" ይላሉ።
በሌላ በኩል መንግሥት በጦርነቱ ምክንያት ዓለም አቀፍ ጫና ሲደርስበት፣ በተለይ በአሜሪካና አውሮፓ ከባድ የዲፕሎማሲ ጫና አጋጥሞታል የሚለው ዳዊት በበኩሉ ይህንን ለመመከት ግን "ከዋና መሥሪያ ቤት በሚሰጠን መመሪያ መሠረት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማስረዳት ስንሰራ ነበር" ብሏል።
ሆኖም ውጤታማ አልሆነም የሚል ድምዳሜ እንዳለው በመግለጽ "በእኔ ግምት የኤምባሲዎቹ መዘጋት ምክንያት ካለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት በተጨማሪ መንግሥት ተገቢውን የዲፕሎማሲ ሥራ አልሰሩም ያላቸውን በአሜሪካና አውሮፓ የሚገኙትን ጨምሮ እንዲዘጉና ዲፕሎማቶቹም እንዲመለሱ አድርጓል" ሲል ያስረዳል።
በዚህ ጉዳይ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተጨማሪ ማብራሪያ ለመጠየቅ ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።
ሆኖም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ወደ ኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች በላከው ደብዳቤ ለሠራተኞቹ አዲስ ስልጠና ለመስጠት እንዲሁም በተሻሻለ አደረጃጀትና የሰው ኃይል ለማጠናከር እንደሆነ ይገልጻል።
ኤምባሲዎችን መዝጋት እና ማዘዋወር ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አዲስ አደለም የሚሉት የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ ከሳምንት በፊት ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ መንግሥት በተለያዩ ዘርፎች የተሃድሶ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አሁን መንግሥት እየወሰዳቸው ያላቸው የተሃድሶ እርምጃዎች ብቃትን መጨመር ላይ ትኩረት ያደረጉ መሆናቸውንም አክለው ተናግረዋል።
እነዚህ ማሻሻያዎች በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እና በኤምባሲዎች እየተካሄደ መሆኑንም ያነሳሉ።
በኤምባሲዎች ውስጥ የሚካሄደው ማሻሻያ ወጪን መቆጠብ እና 'ዲጂታላይዝ' ማድረግ ላይ ያተኮረ መሆኑን አምባሳደሩ ጨምረው ተናግረዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አሁን እያዳረገ ያለው የተሃድሶ እርምጃ "ውጤታማ ዲፕሎማሲያዊ ተቋም" መገንባት መሆኑን በማንሳት አሁን ካለው የትግራይ ጦርነት ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው አብራርተዋል።
የኤምባሲዎቹ መዘጋት የሚፈጥረው ጫና አለ?
ኢትዮጵያ ከኃይለሥላሴ ዘመን ጀምሮ በትልልቅ ዲፕሎማሲያዊ ስኬቶች የምትታወቅ የዓለም ዓቀፍ ተቋማት መስራችና አባል አገር ናት።
በርካታ ዓለም ዓቀፋዊ ስምምነቶች ከፈረሙት መካከል እና በእነዚህም ስምምነቶች የምትገዛ ሆና ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት በማምጣት እውቅ ዲፕሎማቶች በማፍራት ትጠራለች።
የዲፕሎማሲና ዓለም አቀፋዊ ግንኙነቶች ባለሙያው ዳዊት "አሁን ይሄን ሁሉ ስኬት በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ታች ወርዷል፤ ያጋጠመን ችግር ከ50 ዓመታት በላይ የተገነባውን ዲፕሎማሲ የሚያፈርስ ነው" የሚል ቅሬታ አለው።
መሥሪያ ቤቱ በሚቀጥሉት ዓመታት የዲፕሎማሲ አድማስ የማስፋት፣ ተጨማሪ ኤምባሲዎች የመከፈት እንጂ ይሄንን ያክል ቁጥር ያላቸው ሚስዮኖች የመዝጋት ዕቅድ ኖሮት አያውቅም የሚሉት ደግሞ መርከብ ነጋሽ ናቸው።
ሆኖም "አገሪቷ ይሄንን የሚሸከም ኢኮኖሚያዊ አቅም የላትም፤ ይሁን እንጂ ለስብሰባዎችና ሌሎች ጉዳዮች ብዙ ገንዘብ የሚያወጣ መንግሥት ነው" በማለት ውሳኔውን ይተቻሉ።
ሚሲዮኖቹ የአገር ጥቅም ለማስከበር የሚያግዙ ሥራዎች በመስራት እንደቆዩ የሚገልጹት ባለሙያዎቹ ውሳኔው ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የሕዝብ ጥቅም ማስከበር ላይ አሉታዊ ጫና እንዳያሳድር ስጋት አላቸው።
ኤምባሲዎቹ የውጭ ኢንቨስትመንት በመሳብ፣ የአገር ውስጥ ምርቶች በመሸጥና ቱሪዝም መሳብ ላይ ትኩረት አድርገው ሲንቀሳቀሱ ነበሩም ይላሉ።
ነገር ግን ኢትዮጵያ ብዙ ጥቅም የማታገኝባቸው ኤምባሲዎች እንዲሁም ዝቅተኛ አፈጻጸም ያላቸው ሚስዮኖች የሉም ማለት ይቻላል? ስንል ጠይቀናል።
የዲፕሎማሲ ባለሙያው ሰመረ፣ ሲጠና ክፍተት ያለበት አንድ ወይም ሁለት ሊኖር ይችላል፤ በአንዴ 30 ኤምባሲዎች መዝጋት ግን ሌላ ትርጉም ነው ያለው ይላሉ።
"ብዙ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥቅም አይገኝባቸውም የተባሉ አሉ፤ ብዙ ዜጋም የሌላቸው። ሆኖም እነዚህ ጽህፈት ቤቶች በመዝጋት ከሩቅ ውጤታማ ሥራ መስራት አይቻልም። ከዚህ ይልቅ እንዲጠናከሩ በማድረግ መፍትሄ ማምጣት ይቻል ነበር፤ የሚል እምነት አለኝ" ብለዋል።
ይህ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ አለው የሚሉት ባለሙያው፡ "ምክንያቱም እንደምትፈልገው የውጭ ኢንቨስትመንት መሳብ፣ መሸጥ ወይም ከውጭ ማስገባት አይቻልም" ይላሉ።












