በኦሮሚያ ክልል ከ2 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ የምግብ እርዳታ ይፈልጋል ተባለ

በኦሮሚያ ክልል በተፈጠረ የምግብ እጥረት ሳቢያ ከሁለት ሚሊየን በላይ ሕዝብ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ተገለጸ።
የምዕራብ አርሲ እና ጉጂ ዞኖች ነዋሪዎችን ጨምሮ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልገው የገለጸው የኦሮሚያ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ነው።
የኮሚሽኑ ምክትል ኃላፊ አቶ ገራሙ ኦሊቃ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የምግብ እጥረቱ የተከሰተው በተለያዩ ምክንያቶች ነው።
"ሰዎች በኦሮሚያ ክልል በሰው ሰራሽ እና በተፈጥሮ ምክንያቶች ለምግብ እጥረት ይጋለጣሉ" ያሉት ገራሙ፤ "ዘንድሮ በተደረገው ጥናት እራሳቸውን መመገብ የማይችሉና የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ተለይተው ሁለት ሚሊዮን ሰዎች የምግብ እርዳታ እየተደረገላቸው ነው" ብለዋል።
የመሬት መንሸራተት እና ጎርፍ ባሉ ተፈጥሯዊ ምክንያቶች ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር መጨመሩንም ተናግረዋል።
"ለምሳሌ በጉጂ ዞን በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ከ100 ሺህ ባላይ ለሆኑ ሰዎች ድጋፍ እየተደረገ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በጎርፍ እና በደኅንነት ስጋት ከቀያቸው ለተፈናቀሉም ክትትል እየተደረገ ድጋፍ እየቀረበላቸው ነው" ይላሉ።
በጉጂ ዞን በ9 ወረዳዎች ውስጥ በድርቅ እና በደኅንነት እጦት የተነሳ 250 ሺህ የሚሆን ሕዝብ ለምግብ እጥረት መጋለጡን የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ ተሾመ ከበደ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
እንደ ምክትል አስተዳዳሪው ገለጻ ከሆነ የምግብ እጥረቱ ከተከሰተባቸው ወረዳዎች መካከል ጉሚ ኤልዳሎ፣ ሊበን፣ ዋዳራ፣ ጊርጃ፣ አዶላ ሬዴ እና ሰባ ቦሩ ተጠቃሽ ናቸው።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የጉጂ ዞን ነዋሪዎች በዝናብ ወቅት ዘር ቢዘሩም ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ ባለመዝነቡ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ክልል ከፌደራል መንግሥት ከሚያገኘው ድጋፍ ውጪ በተጠባበቂ ከያዘው ፈንድ ለተጎጂዎች ድጋፍ እያቀረበ መሆኑን የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኃላፊው አቶ ገራሙ አስረድተዋል።
የምግብ እጥረቱ ላጋጠማቸው ሰዎች በ75 ሚሊዮን ብር ምግብ ተገዝቶ እየቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።
የኮሚሽኑ ምክትል ኃላፊ በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ የተራድኦ ድርጅቶች ትኩረታቸውን ወደ ሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል እንደሚያደርጉ ቀድሞ በመታወቁ ቅድመ ዝግጅት አድርገን ነበር ይላሉ።
ምንም እንኳን የምግብ እጥረቱ ያጋጠማቸው ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ቢሆንም፤ እስካሁን ድረስ መንግሥት በተቻለው መጠን የምግብ አቅርቦትን በማጠናከር ችግሩ ወደ ረሃብ ደረጃ እንዳይሸጋገር ማድርግ መቻሉን ተናግረዋል።












