ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ ከአፍጋኒስታን በመልቀቂያ ቀነ ገደቡ ምክንያት ግፊት በዝቶባታል
አሜሪካ ከታሊባን ቁጥጥር ስር ካለችው አፍጋኒስታን ለመልቀቅ ተጨማሪ ጊዜ እንድትፈቅድ ግፊት እየተደረገባት ነው።
ከታሊባን ጋር በተደረሰ ስምምነት መሠረት አሜሪካ እስከ አውሮፓውያኑ ነሐሴ 31 ድረስ ከሃገሪቱ ሙሉ ለሙሉ ለቃ መውጣት አለባት።
ፈረንሣይ፣ እንግሊዝ እና ጀርመን ከማክሰኞ የመሪዎች ጉባኤ በፊት ተጨማሪ ጊዜ ይኑር የሚል ሃሳብ አንስተዋል።
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የመልቀቂያ ቀነ ገደቡን በማራዘም ጉዳይ በሚቀጥሉት 24 ሰዓታት እንደሚወስኑ አንድ ባለሥልጣን ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
ታሊባኖች ለቢቢሲ እንዳስታወቁት ቀነ ገደቡ ቢራዘም የተደረሰውን ስምምነት እንደሚጥስ እና የአሜሪካ ኃይሎች ከቆዩ መዘዝ ይኖረዋል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ከአፍጋኒስታን ርዕሰ መዲና ካቡል በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲወጡ ተደርጓል። ሌሎች ደግሞ በአሜሪካ ወታደሮች እና አጋሮቻቸው በሚጠበቀው በከተማዋ አየር ማረፊያ ወይም በአቅራቢያው ይገኛሉ።
ከሸሹት ሰዎች ብዙዎቹ በተለይም ከውጭ ኃይሎች ጋር አብረው ሲሠሩ የነበሩት ሲሆን እአአ ከ 1996 እስከ 2001 ሥልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ ጠንከር ያለ የእስልምና ሕግን የተገበረው ታሊባንን በቀል ፍራቻ ላይ ናቸው።
በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የፈረንሳዩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዣን ይቭስ ለድሪያን "አሜሪካ ያስቀመጠችው የነሐሴ 31 ቀነ ገደብ አሳስቦናል። ቀጣይ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልጋል" ብለዋል።
የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሄይኮ ማስ ደግሞ የካቡል አውሮፕላን ማረፊያ ከተቀመጠው የጊዜ ገደብ በኋላም ክፍት እንዲሆን ከኔቶ አጋሮች እና ከታሊባን ጋር መወያየታቸውን ተናግረዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ከሌሎች የጂ7 መሪዎች ጋር ማክሰኞ በሚደረገው ጉባኤ ወቅት አሜሪካን ቀነ ገደቡን እንድታራዝም ይጠይቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የመከላከያ ሚኒስትሩ ቤን ዋላስ እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "አሜሪካ የምታራዝምበትን መንገድ ለማየት" ይሞክራሉ።
ዩናይትድ ኪንግደም ማንኛውም የውጭ ጦር በካቡል አየር ማረፊያ ያለ የአሜሪካ ወታደሮች መቀጠል አይችልም ብላለች።
ወታደራዊ አማካሪዎች ለኋይት ሃውስ እንደገለፁት ወታደሮቹ ከንብረቶቻቸው እና ከመሣሪያዎቻቸው ጋር በቀነ ገደቡ ለመልቀቅ ማክሰኞ ውሳኔ መስጠት ያስፈልጋል ማለታቸውን ሲኤንኤን ዘግቧል።
የመከላከያ ባለሥልጣን ለመገናኛ ብዙሃኑ እንደተናገሩት ባይደን በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ ለመልቀቅ ከተስማሙ ሰዎችን ለማስወጣት "ጥቂት ተጨማሪ" ቀናት የሚኖሩ ሲሆን ለወታደሮች ደግሞ የሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ሊያስፈልግ ይችላል።
በአሁኑ ወቅት 5 ሺህ ወታደሮች በስፍራው ይገኛሉ።
እንደ ኋይት ሃውስ ገለጻ ሰኞ ዕለት ብቻ 24 ሰዓት ባልሞላ ጊዜ 10 ሺህ 900 ሰዎች ከካቡል ማስወጣት ተችሏል።
ነሐሴ 14 ሰዎችን ማስወጣት ከተጀመረ ወዲህ አሜሪካ 48 ሺህ ያህል ሰዎችን ማስወጣቷን ወይም እንዲወጡ ማመቻቸቱን ኋይት ሃውስ አስታወቋል።
በዋሽንግተን ዱለስ አውሮፕላን ማረፊያ የተነሱ ምስሎች አፍጋኒስታኖች ወደ ሃገሪቱ ሲገቡ ያሳያል።
ታሊባን አፍጋኒስታኖች በሚታረቅ መልኩ ሃገሪቱን እንደገና ለመገንባት እንዲደግፉ ጠይቋል። የታሊባኑ ቃል አቀባይ ሱሃይል ሻሂን ለቢቢሲ እንደገለጹት ፓስፖርት ያላቸው ሰዎች ከተጠቀሰው ቀነ ገደብ በኋላም በንግድ በረራዎች መውጣት እንደሚችሉ ተናግረዋል።
"በአገሪቱ ውስጥ እንዲቆዩ እንፈልጋለን። ለመሄድ ካሰቡ ግን ይችላሉ" ብለዋል።
የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት በአፍጋኒስታን ጉዳይ ላይ ለመወያየት ማክሰኞ አስቸኳይ ስብሰባ ሊያካሄድ አቅዷል። ይህ የሆነው የእርዳታ ድርጅቶች በሃገሪቱ እየተስፋፋ የሄደውን የሰብዓዊ ቀውስ እና የሰብአዊ መብቶችን ጥሰት በተለይም የሴቶች መብቶችን በተመለከተ ማስጠንቀቂያ ከሰጡ በኋላ ነው።
ታሊባኖች የሴቶችን እና የልጃገረዶችን መብት እናከብራለን ቢሉም የእስር እና የግድያ ዘገባዎች እየወጡ ነው። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቶች የተባበሩት መንግስታት ጉዳዩን ለመመርመር ዓለም አቀፍ ገለልተኛ አካል ማቋቋም አለበት ይላሉ።
የማክሰኞ አስቸኳይ የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ስብሰባ ይህንን ማድረግ ቢችልም በፓኪስታን የቀረበው ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ያን ያህል ርቀት አይሄድም ተብሏል።
የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኃላፊ ነገሮችን እንዲከታተሉ እና በታህሳስ ወር ሪፖርት እንዲያደርጉ የውሳኔ ሃሳቡ ይጠይቃል።
አሜሪካ ሃይሎቿን ለማውጣት በደረሰችበት ውሳኔ ታሊባን ሃገሪቱን መቆጣጠሩን ተከትሎ ሰዎችን የማስወጣት ሥራው ተጀመረ።
ታሊባን በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ትግሉን ለመቀጠል ዝግጁ እንደሆኑ ከሚናገሩበት የፀረ-ታሊባን ተቃዋሚዎች ምሽግ ከሆነው እና ከካቡል በስተ ሰሜን ምስራቅ ከሚገኘው የፓንጅሺር ክልል ውጭ መላው ሃገሪቱን ተቆጣጥሯል።
የአልቃይዳን እአአ መስከረም 11/2001 ጥቃቶችን ተከትሎ ታሊባኖች በአሜሪካ እና በአጋሮቿ ከስልጣን ተወግደዋል።ሆኖም ግጭቶች ለ 20 ዓመታት ዘልቀዋል።