በአዲስ አበባ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ሊከተቡ ነው

ታትሟል

በአዲስ አበባ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎችን የመክተብ እቅድ እንዳለ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ አስታወቀ።

በዚህኛው ዙር የሚሰጠው ክትባት ቀደም ሲል ክትባቱን ያልወሰዱ፣ እድሜያቸው 35 ዓመት የሆነ እንዲሁም እድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑና ተጓዳኝ በሽታ ላለባቸው ነዋሪዎች መሆኑ ተገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪ በሥራ ባህርያቸው ተጋላጭ ናቸው ተብለው የተለዩ ከ105 በላይ ለሚሆኑ የመንግሥትና የግል ተቋማት መሆኑንም የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ ማስታወቃቸውን አስተዳደሩ በማኅበራዊ ትስስር ገፁ ላይ ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።

ከእነዚህ የተለዩት ተቋማት መካከል የትራንስፖርት ዘርፍ፣ የግልና የመንግሥት ባንኮች፣ የፌደራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ይገኙበታል ተብሏል።

ከዚህ ቀደም የኮቪድ-19 ክትባት መከላከያ ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ የጤና ባለሙያዎች፣ ዕድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ ለሆኑ እንዲሁም ዕድሜያቸው ከ55 አስከ 64 የሆኑና ተጓዳኝ የጤና ችግር ላለባቸው ብቻ ቅድሚያ እንዲያገኙ ሲደረግ ነበር።

በአሁኑ ወቅት በሰባት ለጋሽ አገራት እገዛ የተለያዩ ክትባቶች ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ የሚገኝ ሲሆን እነዚህም አስትራዜንካ፣ ሲኖፋርምና ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን አገልግሎት ላይ እየዋሉ እንደሚገኝም ዶክተር ዮሐንስ አስረድተዋል።

እነዚህን ክትባቶች አስመልክቶ ኃላፊው ባስተላለፉት መልዕክት "የክትባቶቹ መጠሪያ የተለያየ ቢሆንም በደኅንነታቸዉና ፍቱንነታቸዉ፣ የወረርሽኙን ስርጭት ከመቆጣጠርና በወረርሽኙ ሊደርስ የሚችለውን የከፋ ህመምና ሞት ከመከላከል አንጻር ሁሉም ክትባቶች ተመሳሳይ ዉጤት ያላቸዉ በመሆኑ ማኅበረሰቡ ያለምንም ስጋት ወደ መንግሥት የጤና ጣቢያዎች በመሄድ ክትባቱን በነፃ ያለምንም ክፍያ በመውሰድ ራሱንና ቤተሰቡን ከአስከፊው ወረርሽኝ እንዲጠብቅ" ብለዋል።

በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ከገባበበት ጀምሮ ይህን ያህል የከፋ ጉዳት ባያደርስም ባለፉት አራት ሳምንታት በተለይም በአዲስ አበባ በኮሮናቫይረስ የሚሞቱ፣ ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል የሚገቡ እንዲሁም የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ጭማሪ በማሳየቱ በጣም አሳሳቢ መሆኑንም ዶክተር ዮሐንስ ጠቅሰዋል።

በበርካታ የአፍሪካ አገራት የታየው የወረርሽኙ ሦስተኛ ማዕበል (ሰርድ ዌቭ) በአዲስ አበባ ምልክቶች መታየቱንም አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የሚሞቱ፣ ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል የሚገቡ ሰዎች ቁጥር በአስደንጋጭ ሁኔታ መጨመሩን ተከትሎ ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያግዝ የተሻሻለ መመሪያ መውጣቱ ከሰሞኑ ተገልጿል።

በተሻሻለው መመሪያ መሰረት ከስድስት ዓመት በላይ የሆኑ ህፃናት የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ እንዲያደርጉ፣ በሠርግ፣ በቀብር እንዲሁም በስብሰባዎች ላይ የሚገኙ ሰዎች ብዛት ከአምሳ እንዳይበልጥ፣ በካፌዎችና በሬስቶራንቶች ውስጥ በአንድ ጠረጴዛ ላይ ከሦስት ተገልጋዮች በላይ እንዳይቀመጡ የሚሉና ሌሎች ዝርዝሮች ተካትተውበታል።

የጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያወጡት ይህ መመሪያ ከነሐሴ 13/2013 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል።