ከሐሮማያ ዩኒቨርስቲ በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቀችው እና የአርብቶ አደር ሴቶችን ማገዝ የምትፈልገው ኦብሲቱ ዱባ

ኦብሲቱ ዱባ
ታትሟል

ኦብሲቱ ዱባ ትባላለች። ተወልዳ ያደገችው ቦረና ያቤሎ ነው። ትምህርቷን እስከ 12ኛ ክፍል እዚያው ነው የተማረችው።

በሐሮማያ ዩኒቨርስቲ ከሕግ ትምህርት ክፍል በከፍተኛ ማዕረግ ተመርቃለች።

"በዩኒቨርስቲ ቆይታዬ 3.91 አጠቃላይ ውጤት አስመዝግቤ ነው ያጠናቀቅኩት" የምትለው ኦብሲቱ አሁን ደግሞ በዚያው ዩኒቨርስቲ በመምህርነት ተቀጥራ እየሰራች ነው።

"የቦረና ሴቶች በተለይ የአርብቶ አደር ልጆች፣ ጠንክረው እንዲወጡ ምሳሌ መሆን እፈልጋለሁ ትላለች" ኦብደሲቱ ዱባ።

የ2021 የኦሮሞ ጥናት ማሕበር (ኦሳ) የጠንካራ ተማሪ ሽልማትን የተቀበለችው ኦብሲቱ፣ የሕይወት ውጣ ውረዷን፣ ልምዷን እና ገጠመኞቿን እንዲሁም ስለተበረከተላት እውቅና ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርጋለች።

ጠንካራ ተማሪ ተብሎ እውቅና ማግኘት

በዚህ ዓመት የኦሮሞ ጥናት ማሕበር ሦስት እውቅናዎችን ነው የሰጠው። በጠንካራ ተማሪ ዘርፍ ያሸነፈችው ደግሞ ኦብሲቱ ዱባ ናት።

በማህበሩ በእጩነት ስለቀረበችበት መንገድ ስትናገር "እኔ በከፍተኛ ውጤት ተመርቄ ፎቶግራፉ በማህበራዊ ሚዲያ በከፍተኛ ሁኔታ ሲዘዋወር ነበር።" ትላለች።

ከዚያም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ዶ/ር ፍሬሕይወት ጀቤሳ የሚባሉ ግለሰብ ዜናውን አይተው ፈልገው ካገኟት በኋላ፣ ስለራሷ ጥቂት ነገር እንድታዘጋጅ እንደነገሯት ትገልጻለች።

ከዚያ በኋላ በእርሳቸው በኩል እጩ ሆና ቀረበች።

ማህበሩ ያላትን ልምድና የትምህርት ሁኔታ ከሌሎች እጩዎች ጋር ከገመገመ በኋላ ማሸነፏን ነገሯት።

የኦሳ መድረክ ትልቅ መድረክ ነው የምትለው ኦብሲቱ፣ በመድረኩ የትልልቅ ሰዎች ስም እንደሚነሳ ትጠቅሳለች።

"በእንደዚህ ዓይነት መድረክ ላይ የኔ ስም በመነሳቱ ከፍተኛ ደስታ እና ትልቅ የኃላፊነትት ስሜት ተሰምቶኛል።" ብላለች።

ኦብሲቱ ዱባ በምረቃ ጋወን የተሸለመችውን ዋንጫ ይዛ

የፎቶው ባለመብት, Obsituu Duubaa

ተግዳሮት

"እኔ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ በነበርኩበት ወቅት ጠንካራ ተማሪ ነበርኩ" የምትለው ኦብሲቱ ፣ ዩኒቨርስቲ ውስጥ አንድ ሴሚስተር ከፍተኛ ውጤት አምጥቶ በቀጣዩ ሴሚስተር መድከም በሌሎች ዘንድ መልካም አስተያየት እንደማያሰጥ ትናገራለች።

ይህንንም በአሸናፊነት ለመወጣት "ጥንካሬዬን ለማሳመን አምስቱንም ዓመት ትንቅንቅ አድርጌያለሁ" ትላለች።

ከፍተኛው የሴቶች ተግዳሮት የአመለካከት ችግር ነው ያለችው ኦብሲቱ፣ "ሴቶች ሰርተው አሳይተው ማሳመን አለባቸው።" ስትል ሃሳቧን ታጠናክራለች።

በትምህርት እና ጥናት ላይ መስራት እና የአርብቶ አደር ልጆችን ማነቃቃት የምትፈልገው ኦብሲቱ "የአካዳሚ ሰው መሆን እፈልጋለሁ" ስትል የወደፊት ዓላማዋን ገልጻለች።

በርትተው ከሰሩ ስኬታማ መሆን እንደሚቻል በተጨባጭ ማሳየት እንደምትፈልግም ተናግራለች።

ከእኔ የበረቱ ጠንካራ ሴቶች ከቦረና እንዲወጡ መንገድ ማሳየት እፈልጋለሁ የምትለው ኦብሲቱ፣ "የሰብዓዊ መብት አቀንቃኝ የመሆን ፍላጎት አላት።

"የነገሮች አለመሟላት፣ ሴት መሆን፣ ከስኬት እንደማያግድ ማሳየት እፈልጋለሁ። በተለይ የአርብቶ አደር ሴት ልጆችን ማገዝ፣ ልበ ሙሉ እንዲሆኑ እና እንዲጠነክሩ ወደፊት ማገዝ እፈልጋለሁ።" ትላለች ኦብሲቱ።

"ወንድ ፈጽሞት እኛ የማንችለው አንድም ነገር የለም።" የምትለው ኦብሲቱ፣ ሴት ልጆች ሁሉንም ማድረግ እንችላለን በማለት ሴቶች በራስ በመተማመን ወደ ፊት እንዲሄዱ መክራለች።

በሕይወትሽ ምሳሌ የሆነሽ ማን ነው?

"ለኔ ምሳሌዬ እናቴ ናት። እናቴ ብቻዋን ስላሳደገችኝ፣ ሌላው ሰው ከሚለው በላይ በሁሉም መስክ ምሳሌዬ ነች። ከአባቴ ጋር አላደግኩም። ቤት ውስጥም የወንድና የሴት ድርሻ የሚባለውን ነገር አላወቅኩም። ስብሰባ ከተጠራ ከእኛ ቤት ስብሰባው ላይ የምትገኘው እናቴ ናት።" ትላለች።

ኦብሲቱ እናቷ ገቢ በማምጣት የቤቱ ካስማ ሆነው መኖራቸውን ታስታውሳለች።

ያን ሁሉ እያየች በማደጓ ሴት ሁሉንም ማድረግ ትችላለች የሚል አስተሳሰብ በውስጧ እንዳስቀረ ተናግራለች።

በዚህም የተነሳ "ሴት በመሆኔ የሚቸግር ነገር እንደሌለ አውቄያለሁ" የምትለው ኦብሲቱ፤ እናቷ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ሳለች ቢሞቱም "ሁሉንም ነገር ማለፍ እንችል አድርጋ አሳድጋኛለች።" ስትል ስለ እናቷ ታስረዳለች።

ያለኝን በራስ መተማመን የተማርኩት ከእናቴ ነው በማለትም "በእኔም ትተማመን ነበር። እርሷ እንደምትፈልገው ሆኜ፣ ኖራ ብታየኝ ደስ ይለኝ ነበር። ግን ፈጣሪ እንዳለው ነው የሚሆነው" በማለት ሃሳቧን አጠቃላለች።