ኮሮናቫይረስ፡ የቻይና ትልቁ ወደብ በከፊል መዘጋት ዓለም አቀፍ የምርት አቅርቦት ላይ ሥጋት ፈጠረ

የፎቶው ባለመብት, VCG
በኮሮናቫይረስ ምክንያት ከቻይና ትልቁ የጭነት ወደቦች መካከል አንዱ በከፊል መዘጋቱ በዓለም ንግድ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል የሚል አዲስ ሥጋት ፈጠረ።
ኒንግቦ ዦሻን በሚባለው በዚህ ወደብ አንድ የወደቡ ሠራተኛ 'ዴልታ' በተሰኘው የኮቪድ-19 ዝርያ በመያዙ ረቡዕ ዕለት በወደቡ ተርሚናል የሚሰጥ አገልግሎት ዝግ ተደርጓል።
ኒንግቦ ዦሻን በምሥራቅ ቻይና የሚገኝ ሲሆን በዓለማችን ሦስተኛው ሥራ የሚበዛበት የጭነት ወደብ ነው።
ኒንግቦ ዦሻን ወደብ መዘጋቱም ወሳኝ የሆነው የገና በዓል ግብይት ከመጀመሩ በፊት የአቅርቦት ሰንሰለቱን ሊያቋርጥ ይችላል ተብሏል።
ሌላ ማስታወቂያ እስኪነገር ድረስ በሜሻን ደሴት ላይ የሚገኘው ወደብ መዘጋት የወደቡን የኮንቴኔር ጭነት የመያዝ አቅም በሩብ እንደሚቀንሰው ተነግሯል።
እንደ የማጓጓዣ ዋጋ ታሪፍ መረጃ የሚሰጠው ፍሬግቶስ ባልቲክ ግሎባል ኮንቴይነር ፍሬይት ኢንዴክስ (ኤፍቢኤክስ) ከሆነ፤ ከቻይና እና ከደቡብ ምሥራቅ ቻይና ወደ አሜሪካ ምሥራቃዊ ዳርቻ የማጓጓዣ ዋጋ ቀድሞውኑ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል።
አንዳንድ የዩናይትድ ኪንግደም ንግዶችም በከፍተኛ የማጓጓዣ ክፍያው ሳቢያ ተፅዕኖው አርፎባቸዋል።
የኦሽን ሽፒንግ አማካሪ የሆኑት ጀሰን ቺያንግ ለመጪዎቹ በርካታ ወራትም ወረርሽኙ የዓለም የማጓጓዣ ኢንደስትሪ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል ሲሉ ለቢቢሲ እስያን ቢዝነስ ሪፖርት ተናግረዋል።
"እስከ ሁለት ዓመት ድረስ አዲስ የማጓጓዝ አቅም እናያለን ብለን አንጠብቅም፤ ከአሁን ጀምሮ እስከ ሁለት ዓመት ያለው ጊዜ በወረርሽኙ ሁኔታ የሚወሰን ነው" ብለዋል ጀሰን።
ኒንግቦ ዦውሻን ከሻንጋይ እና ሲንጋፖር ቀጥሎ የዓለማችን ጥልቁ የጭነት ወደብ ነው።












