ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ልጇን ለሞት አጋልጣ ለስድስት ቀናት ልደቷን ስታከብር የነበረች እናት በቁጥጥር ስር ዋለች
ልጇን ብቻዋን ለርሃብ አጋልጣ ለስድስት ቀናት ልደቷን ስታከብርና ስትጨፍር የነበረችን እናት ፖሊስ አሰሯል።
በእንግሊዝ ቨርፊ ኩዲ የተባለችው እናት እንደ አውሮፓውያኑ በ2019፣ 18 ኛ ልደቷን ለማክበር የ20 ወር ልጇን አፓርትመንት ውስጥ ለ6 ቀናት ብቻዋን ትታ መሄዷን አምናለች፤ ጨቅላዋም ህይወቷ አልፏል።
"ግድየለሽ" በመሆን ልጄን ትቼ ወደ ለንደን እና ኮቨንትሪ ተጉዣለሁ ስትል ለሉዊስ ክራውን ፍርድ ቤት ተናግራለች።
የፍርድ ቤቱ ዳኛ ክሪስቲን ላንግ "ህጻኗ ፍላጎቷን ማሟላት የማትችልና ሙሉ በሙሉ የእናቷን ድጋፍ የምትሻ" ረዳት የሌላት ሕፃን ነበረች ብለዋል።
ልደት ለማክበር በሚል ልጅን ለስቃይ አጋልጦ መሄድ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው ሲሉም ዳኛዋ አክለዋል።
አቃቤ ህግ በበኩሉ ህጻኗ ልጅ ለአምስት ቀናት ከ 21 ሰዓታት ከ 58 ደቂቃዎች በቤቱ ወልል ላይ ብቻዋን ሆና የሚያሳይ በድህንነት ካሜራ የተቀረጸ ማስረጃ እንዳለው ለፍርድ ቤት አስረድቷል።
ኩዲ ልጇን ቤት ውስጥ ትታ ወደ ለንደን ሄዳ የልደት ቀንዋን ከወንድ ጓደኛዋ ጋር ማሳለፏ ነው የተነገረው።
ከሁለት ቀናት በኋላ ደግሞ በደቡብ ምስራቅ ለንደን ውስጥ ኤሌፋንት እና ካስል ውስጥ የሙዚቃ አጫዎች [ዲጄ] ልደቷን ለታዳሚያን ባበሰረበት ኮንሰርት ላይ መገኘቷን ለፍርድ ቤቱ ተናግራለች።
ይህ ከሆነ ከቀናት በኋላ ደግሞ ወደ ሌላ የልደት ፕርግራም ሄዳለች ከዚያም ከስድስት ቀናት በኋላ ወደ ቤቷ መመለሷንም አስረድታለች።
ኩዲ ቤቷ ስትደርስ ወደ አደጋ ጊዜ ጥሪ ማዕከል ደውላ ለሕክምና ባለሙያዎች ልጇ ከእንቅልፉ መንቃት እንዳልቻለች ገልጻለች።
ታዲያ የህክምና ቡድን ወደ ቤቷ ሲደርሱ ኩዲ የተረበሸችና መረጋጋት ያቃታት ሆና እንዳገኟት ለፍርድ ቤት ተብራርቷል።
የሕክምና ባለሞያዎች አሲያ የተሰኘችውን ልጅ የሕፃናት ሆስፒታል በፍጥነት መወሰዷን እና እዚያ እንደደረሰች ወዲያውኑ እንደሞተች የክራውን ዐቃቤ ሕግ አገልግሎት ገልጿል።
አሲያ ላይ ምርመራ ከተደረገ በኋላ የህልፈቷ መንስኤ ረሃብ፣ የውሃ እጥረት እና ኢንፍሉዌንዛ መሆኑን ሆስፒታሉ አስረድቷል።
"የአሲያ እናት ልጇን ከጉዳት የመጠበቅ ግዴታ ቢኖርባትም በራስ ወዳድነት የራሷን ፍላጎት ማስቀመጥን እና ከጓደኞ ጋር መሆንን ከምንም በላይ መረጠች" ሲሉ አንድ የሆስፒታሉ ባልደረባ ተናግረዋል።
"የድርጊቷ ውጤት አስያ ብቻዋን በቤቱ ውስጥ በነበረችባቸው ቀናት እና ሌሊቶች ውስጥ ከባድ ሥቃይ እንዲደርስባት አድርጓል። ይህ ቀደም ሲል የተጣሉ እና ችላ የተባሉ በርካታ አጋጣሚዎችና ታሪኮችን ተከትሎ መጥቷል" ሲሉ አክለዋል።
ኩዲ ለመጀመሪያ ጊዜ ለፖሊስ የእምነት ክህደት ቃሏን ስትሰጥ አንድ ወደ ለንደን ካደረገችው አንድ ጉዞ በስተቀር ሁሉንም ጊዜ ከልጅዋ ጋር በአፓርታማው ውስጥ እንደነበረች ትናገራለች።
ሆኖም ከዚህ ቃሏ በተቃራኒ የፖሊስ መኮንኖች የ ደህንነት ካሜራ [CCTV] ቀረፃንና እንዲሁም ከቤቷ ርቃ በነበረችበት ጊዜ ስትዝናና የሚያሳዩና በስልክ የተቀረጹ ቪዲዮችን አግኝቷል።
"በሁኔታው አዝነናል። እንደ ቤተሰብ ብዙ ያልተመለሱ ጥያቄዎች አሉን። ቨርፊ በዕድሜዋ ብዙ ገጥሟታል። እሷን ለመደገፍ የምንችለውን ሁሉ አድርገናል" ሲሉ የኩዲ ቤተሰቧች በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል።
"ቤተሰቡ ሊቋቋመው በማይችለው ሀዘን ውስጥ ነው። ዛሬ በሆነው ነገር ብቻ ሳይሆን ተወዳጇን አሲያን በማጣታችንም እናዝናለን"ሲሉም አክለዋል።