ሱዳን ከኢትዮጵያ 1 ሺህ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለመግዛት እንደጠየቀች ተገለጸ

ታትሟል

ሱዳን አንድ ሺህ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ከኢትዮጵያ ለመግዛት እየተነጋገረች እንደምትገኝ የአገሪቱ ዜና ወኪል ሱና ዘገበ።

የሱዳን የኢነርጂ እና ነዳጅ ሚንስትር ኢንጂነር ጄደን አሊ ኦቢድን ጠቅሶ ሱና እንደዘገበው፤ ሱዳን 1 ሺህ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለመግዛት ከኢትዮጵያ ጋር ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ባለሥልጣን ባለሙያዎች ባለፈው ወር ካርቱም ሄደው የኤሌክትሪክ መስመር ለመዘርጋት የሚያስፈልገውን የግንባታ ጥናት እንዳደረጉ ሚንስትሩ ተናግረዋል።

የሱዳን ባለሙያዎች በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ አቅንተው የሁለቱ አገራት ንግግር እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።

ሱዳን ከዚህ ቀደም ወደ 200 ሜጋ ዋት የሚጠጋ የኤሌክትሪክ ኃይል ከኢትዮጵያ እንደገዛችና ይህም የሱዳንን 10 በመቶ የኤሌክትሪክ ፍላጎትን እንደሚሸፍን የሱና ዘገባ አመልክቷል።

ይህ የኤሌክትሪክ ኃይል በሱዳን ለዕለታዊ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው ነውም ተብሏል።

የሱዳኑ ሚንስትር እንዳሉት፤ ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል የመግዛት እቅድ ሱዳን ከምሥራቅ አፍሪካ አገራት ጋር የምታደርገው የንግድ ትስስር አንዱ መገለጫ ነው። የንግድ ትስስሩ በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጎማ የሚደገፍ እንደሆነ መግለጻቸው ተዘግቧል።

ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ከምትሸጥላቸው አገሮች መካከል ሱዳን እና ጂቡቲ ይጠቀሳሉ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሲጠናቀቅ የሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል የአገር ውስጥ የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ከመሸፈን ባሻገር የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ እንደሚስፋፋም ይጠበቃል።

በሐምሌ ወር ሁለተኛው ዙር የግድቡ የውሃ ሙሌት በአጭር ጊዜ የተጠናቀቀ ሲሆን በቅርቡም በተወሰኑ ተርባይኖች አማካይነት በከፊል ኃይል ማመንጨት እንደሚጀመር ተነግሯል።

ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ በሕዳሴ ግድቡ ግንባታ ላይ እስካሁን ድረስ ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ ስምምነት ላይ አልደረሱም።

በቅርቡ የግድቡን ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በተመለከተ በሦስቱ አገራት የተፈጠረውን ውዝግብ የመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት እንዳስተናገደ አይዘነጋም።