የአፍጋን መንግሥት የታሊባን ጦርን ለመውጋት ነዋሪዎች ከተማ ለቀው እንዲወጡ አሳሰበ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በታሊባን የተያዘችውን ከተማ ለማስለቀቅ መንግሥት የጦር ኦፕሬሽን ከመውሰዱ በፊት ነዋሪዎች ከተማዋን ለቀው እንዲወጡ የመንግሥት ጦር መሪ አሳሰቡ።
በደቡባዊው ሄልማን ግዛት ከታሊባን ጋር የሚደረገውን ውጊያ የሚመሩት ጀኔራል ሳሚ ሳዳት ሰዎች ዋና ከተማዋ ላሽካር ጋህን በተቻለ ፍጥነት ለቀው እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
በላሽካር ጋህ ባለፉት ቀናት በተካሄደ ጠንካራ ውጊያ ቢያንስ 40 ሲቪሎች ተገድለዋል ብሏል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት።
ታሊባኖች አብዛኛውን የከተማዋን ክፍል እንደያዙ ተዘግቧል።
በታሊባን እና በአፋንጋኒስታን መንግሥት መካከል ውጊያው የቀጠለ ሲሆን የመንግሥት ኃይሎች አካባቢው በታጣቂዎች እጅ እንደማይወድቅ ቃል ገብተዋል።
ጄኔራል ሳዳት ለከተማዋ ነዋሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት ሠራዊቱ "አንድም የታሊባን ታጣቂን በሕይወት አይተዉም" ብለዋል።
"ቤቶቻችሁን ለቃችሁ መውጣታችሁ በጣም እንደሚከብዳችሁ አውቃለሁ፤ ለእኛም ከባድ ነው። ለተወሰኑ ቀናት ከተፈናቀላችሁ እባካችሁ ይቅር በሉን።" ብለዋል።
ጄኔራል ሳዳት ቀደም ሲል ለቢቢሲ እንደገለፁት የመንግስት ኃይሎች ከያዙት መሬት ቢለቁም ታሊባን ጥቃታቸውን መቋቋም እንደማይችል ያምናሉ።
የታሊባን በሄልማን ግዛት የሚያደርገው ጥቃት በመላው አፍጋኒስታን የሚያከናውነው ትልቅ ጥቃት አካል ነው።
የአሜሪካ ወታደሮች ከ20 ዓመታት ወታደራዊ እንቅስቃሴ በኋላ ከአፍጋኒስታን ለቀው በመውጣታቸው ታጣቂዎቹ ባለፉት ወራት ፈጣን ግስጋሴ አድርገዋል።
ሔልማን የአሜሪካ እና የእንግሊዝ ወታደራዊ ዘመቻ ዋና አካል ስትሆን ታሊባን የሚያስመዘግበው ማንኛውም ድል ለአፍጋኒስታን መንግሥት ጉዳት ይሆናል።
'በመንገድ ላይ አስከሬኖች'
ታሊባን በአሜሪካ እና በአፍጋኒስታን መንግሥት ጥምረት የአየር ጥቃት እየደረሰበት ሲሆን የከተማዋ ነዋሪዎች በፍርሃት ውስጥ እንዳሉ ይናገራሉ።
"ታሊባንም አይምረንም፤ መንግሥትም የቦምብ ጥቃቱን አያቆምም። መንገዶች ላይ አስከሬኖች አሉ። ሲቪሎች ይሁኑ ታሊባኖች አናውቅም" ሲሉ አንድ ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሌላኛው ደግሞ "የት መሄድ እንዳለብኝ አላውቅም፣ በከተማው ሁሉ ግጭቶች አሉ" ብሏል።
በአፍጋኒስታን የተባበሩት መንግሥታት የእርዳታ ተልዕኮ (ኡናማ) በበኩሉ የታሊባን የመሬት ጥቃትን እና የአፍጋኒስታን የአየር ጥቃቶች ከፍተኛ ጉዳት በማድረሳቸው ሲቪሎች የውጊያውን "ከባድ ሸክም" እንደሚይዙ ገልፀዋል።
በከተሞች ውስጥ የሚደረገውን ውጊያ በአስቸኳይ ማቆምንም ጨምሮ ሁለቱም ወገኖች ሰላማዊ ሰዎችን ለመጠበቅ የበለጠ ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።
ከሟቾች በተጨማሪ በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች መቁሰላቸውን እና በሺህዎች የሚቆጠሩ መፈናቀላቸውን ኡናማ ገልጿል።
በላሽካ ጋህ ያሉ ዶክተሮች ችግሩ ከአቅማቸው በላይ መሆኑን እና የአቅርቦት እጥረት እንዳለባቸው ተናግረዋል። አንድ ሐኪም ለቢቢሲ "በየአቅጣጫው ውጊያ አለ" ብለዋል።












