ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቻይና የበይነ መረብ ጨዋታዎችን 'የኤሌክትሮኒክ ዕጾች' ብላ ከፈረጀች በኋላ የአክስዮን ዋጋ አሽቆለቆለ
የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ሁለት የቻይና ታላላቅ የበይነ መረብ ጨዋታዎችን (ጌም) "የኤሌክትሮኒክ ዕጾች" ብለው ከጠሯቸው በኋላ የኩባንያዎቹ አክሲዮኖች አሽቆልቁሏል።
የቴንሴንት እና የኔትኢዝ አክሲዮኖች በሆንግ ኮንግ የአክስዮን ገበያ ከ10 በመቶ በላይ ቀንሰው ነበር ተብሏል።
ቤጂንግ ኩባንያዎች ላይ እርምጃ መውሰዷ ባለሃብቶችን እያሳሰባቸው ነው።
ከቅርብ ወራት ወዲህ ባለሥልጣናት በቴክኖሎጂ እና በግል ትምህርት ኩባንያዎች ላይ ልጓም ለማጥበቅ ተከታታይ እርምጃዎችን አስተላልፈዋል።
በመንግስት የሚተዳደረው የኢኮኖሚ ኢንፎርሜሽን ዴይሊ ላይ የታተመ አንድ ጽሑፍ ብዙ ታዳጊዎች በበይነ መረብ ጌሞች ሱስ እንደተያዙ እና አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ገልጿል። የዜና ማሰራጫው ከኦፊሴላዊው የዢኑዋ የዜና ወኪል ጋር ትስስር ያለው ነው።
ጽሑፉ የቴንሴንትን ኦነር ኦፍ ኪንግስ የተሰኘ ጌምን በመጥቀስ ተማሪዎች በቀን እስከ ስምንት ሰዓታት እንደሚጫወቱ በመግለጽ በኢንዱስትሪው ላይ ተጨማሪ ገደቦችን እንዲጣል ጠይቋል።
የበይነ መረብ ጌሞችን ከ "መንፈሳዊ ኦፒየም" ጋር ከማመሳሰሉ በፊት "ማንኛውም ኢንዱስትሪም ሆነ ስፖርት ትውልድን በሚያጠፋ መንገድ እንዲያድግ አይፈቀድም" ብሏል።
ቴንሴንት ልጆች ኦነር ኦፍ ኪንግስ የተሰኘው ጌሙን በቀላሉ እንዳያገኙት እና በጨዋታው የሚያሳልፉትን ጊዜ ለመቀነስ አዳዲስ እርምጃዎችን እንደሚያስተዋውቅ ተናግሯል። ኩባንያው ፖሊሲውን በሁሉም ጌሞች ላይ ለማስተላለፍ ማቀዱን ተናግሯል።
ቴንሰንት በዓለም ዙሪያ ካሉ የሙዚቃ ባለመብቶች ጋር ያለው የሙዚቃ ፈቃድ ስምምነቶችን እንዲያቆም ከታዘዘ በኋላ አክሲዮኖቹ ወርደዋል።
እርምጃው የቴክኖሎጂ ኩባንያው በአገሪቱ ውስጥ የበይነ መረብ ሙዚቃ ላይ ያለውን የበላይነትን ለመቋቋም የታለመ ነው። እአአ በ2016 ከተገዛ በኋላ የቻይና ብቸኛ የሙዚቃ ማሰራጨት መብቶችን ከ 80 በመቶ በላይ ይቆጣጠራል።
አዲሶቹ መመሪያዎች በኢንዱስትሪው የውጭ ኢንቨስትመንትንም ገድበዋል።
የፖሊሲው ዋነኛ ለውጥ የመጣው ባለሥልጣናት ልጆችን የማሳደግ የገንዘብ ጫና ለማቃለል ሲሞክሩ ነው።
የቻይና የቅርብ ጊዜ የሕዝብ ቆጠራ እንደሚያሳየው በሰባት አሥርተ ዓመታት ውስጥ የወሊድ ምጣኔ ወደ ዝቅተኛው ደረጃ በመውረዱ ባለሥልጣናት ተጨንቀዋል።
በአገሪቱ 120 ቢሊዮን ዶላር በሚያንቀሳቅሰው የግል የትምህርት ዘርፍ አንዱ ትልቁ የለውጥ ሥራ ነው።