ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የትግራይ ጦርነት መስፋቱን ተከትሎ በኢትዮጵያ የተፈጠሩ ስጋቶች
- ፀሐፊ, ቪቬኔ ኑኒስ
- የሥራ ድርሻ, የቢቢሲ አፍሪካ ዘጋቢ
- ታትሟል
በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ተከትሎ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት አደጋ ላይ እንዳይጥለው እየተሰጋ ነው።
ዘጠኝ ወራትን ያስቆጠረውና በትግራይ አማጺያንና በኢትዮጵያ መከላከያ መከላያ ሠራዊት መካከል የሚካሄደው ጦርነት እስካሁን ድረስ በትግራይ ክልል ብቻ የተወሰነ ነበር።
ነገር ግን ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ጦርነቱ ወደ አፋር እና አማራ አጎራባቾ ክልሎች እየተዛመተ መጥቷል።
ይህ ጦርነት መልኩን ቀይሮ በዚህ መልኩ መቀጠል የያዘው የመንግሥት ኃይሎች ክልሉን ለቅቀው ከወጡ በኋላ የትግራይ አማጺያኑ የክልሉን ዋና ከተማ መቀለን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ ነው።
ይህ ደግሞ በትግራይ ያለው ቀውስ እየተባባሰ ስለመሆኑ ማሳያ ተደርጎ ሊቆጠር የሚችል ሲሆን በአገሪቱ ያለው ብቸኛው ግጭት ግን አይደለም።
በኢትዮጵያ ትልቁ ከሆነው ኦሮሚያ ክልል የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን የመጡት ከሦስት ዓመታት በፊት ነበር። በወቅቱ በርካታ ማሻሻያዎችንና እርምጃዎችን ወስደዋል።
ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስተዋወቁት አዲስ ሥርዓት ቀድሞ የነበረውን ብሔርተኝነት እንዲያገረሽ አድርጎታል። በርካታ ቡድኖችም የራሳችን መሬትና ስልጣን ይገባናል የሚሉ ጥያቄዎችን በተደጋጋሚ እያነሱ ነው።
"ብሔርን መሰረት ያደረገ ጦርነት በብዛት ይታያል" ይላሉ ናይሮቢ ሚገኙት የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ተንታኙ ራሺድ አብዲ።
በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ አለመረጋጋት የሚታይበት ሌላኛው ክልል ቤኒሻንጉል ነው። ክልሉ ከሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ጋር የሚዋሰን ሲሆን ታኅሣሥ ወር ላይ በክልሉ በተፈጸሙ ጥቃቶች ከ2 ሺህ በላይ ሰዎች ተገድለዋል።
ባለፈው ሳምንት ደግሞ የክልሉ ባልስልጣናት ብሔርን መሰረት ያደረግ ግጭት ሲያነሳሱ ነበሩ ያሏቸውን ከ100 በላይ ታጣቂዎችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ገልጸዋል።
ሌላኛው ኢትዮጵያ ላይ የተደቀነው ፈተና ደግሞ ለዓመታት የዘለቀው ከሱዳን ጋር የሚነሳው የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ነው። አገራቱ የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሱበት አካባቢ ለም መሬት ያለውና ለግብርና ምቹ የሆነ ቦታ ነው።
ከትግራይ ጦርነት ጎን ለጎን የኢትዮጵያ መንግሥት በዚሁ ጉዳይ ከሱዳን ጋር መለስተኛ የሚባሉ ግጭቶች ውስጥ ገብቷል።
"ከዚህም በላይ የከፋ ጦርነት ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን እስካሁን አልሆነም" ይላሉ ራሺድ።
በሌላ በኩል ባለፈው ሳምንት ከ1 ሺህ በላይ የሚሆኑ የቅማንት ተወላጆች በአማራ ክልል የሚደረገውን ጦርነት በመሸሽ ወደ ሱዳን ሸሽተዋል። ሽሽታቸውም ከአማራና በትግራይ ኃይሎች መካከል የሚደረገውን ጦርነት ለማምለጥ እንደሆነ የሱዳን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
የአማራ ክልል ባለስልጣናት ባለፉት አስርት ዓመታት የትግራይ ኃይሎች ብሔርን መሰረት ያደረገ ግጭት በማስነሳት የሚከሷቸው ሲሆን የትግራይ ባለስልጣናት ግን ይህንን ይቃወማሉ።
ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በሶማሌ እና አፋር ክልሎች መካከል ያለው ለዓመታት የቆየ አለመግባባትም አለ። ሁለቱም ክልሎች ለኢትዮጵያ እጅግ ወሳኝ ከሆነችው ጅቡቲ በቅርብ ርቀት መገኘታቸው ደግሞ ነገሮችን ይበልጥ አሳሳቢ ያደርጋቸዋል።
"ኢትዮጵያ በታሪኳ ፈተናዎችን በጽናት የማለፍና አንዳንዴ ደግሞ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ የመግባት አጋጣሚዎች ይታዩባታል። ይሄኛው ደግሞ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ነው" ይላሉ መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው 'ወርልድ ፒስ ፋውንዴሽን' ዋና ኃላፊ የሆኑት አሌክስ ደ ዋል።
አንዳንድ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎች ደግሞ አገሪቱ የመበታተን አደጋ ላይ እንደሆነች በተደጋጋሚ እየገለጹ ነው።
"ኢትዮጵያ ትልቅ የሕልውና አደጋ ላይ ስለመሆኗ ምንም ጥርጥር የለውም'' ይላሉ ራሺድ።
"በትግራይ ክልል የተከሰተው ቀውስ እና በሌሎች አካባቢዎች ያለው አለመረጋጋት አገሪቱን ወዴት እንደሚወስዳት መገመት ቀላል አይደለም፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ በጣም ፈታኝ ሁኔታ ላይ መሆኗ ግን አጠያያቂ አይደለም።"
በሌላ በኩል በጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ምንይችል መሰረት ግን "ኢትዮጵያ ስጋት ላይ አይደለችምም፤ የመፈራረስ አደጋም አልተጋረጠባትም" ይላሉ።
"በአሁኑ ጊዜ ስለእንደዚህ አይነት ነገሮች ማውራት በራሱ ተገቢ አይደለም። ከትግራይ በስተቀር አገሪቱን የሚቆጣጠርና ሥራውን በአግባቡ የሚሰራ መንግሥት አለን" ብለዋል።
አክለውም በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰው ጦርነት እንደውም የአገሪቱን ሕዝቦች ወደ አንድ መድረክ ያመጣና አገራዊ አንድነትን የጨመረ እንደሆነ ገልጸዋል።
ባለፍነው ሳምንት የፌደራል መንግሥቱ የተናጠል ተኩስ አቁም ማወጁን ተከትሎ ባለ ሰባት ነጥብ ቅድመ ሁኔታዎችን አቅርበው የነበሩት የትግራይ ኃይሎች በድርድር ላይ የተመሰረተ ተኩስ አቁም ለማድረግ የተሻሻለ አዲስ ቅድመ ሁኔታ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያን ጦር ጨምሮ የክልል ኃይሎችና የኤርትራ ጦር ከክልሉ እንዲወጣ ከመጠየቅ በተጨማሪ በተሻሻለው ቅድመ ሁኔታም ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ፍላጎቱን አለኝ ያለው ህወሓት፤ ዳግም ባወጣው የተኩስ አቁም ቅድመ ሁኔታ ላይ የተከሰተውን ችግር ለመፍታት ሁሉን አቀፍ ፖለቲካዊ ውይይት እና የሽግግር ሂደት እንዲካሄድ ጥሪ አቅርቧል።
በዋነኛነትም በትግራይ ተቋርጠው የቆዩ እንደ ኤሌክትሪክ፣ ቴሌኮምዩኒኬሽን፣ የባንክ፣ የትራንስፖርት፣ የጤና እና የንግድ እንቅስቃሴዎች በፍጥነት መጀመር አለባቸው ይላል።
የትግራይ ክልል በመታገዷ ምክንያት ዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶች አስፈላጊውን እርዳታ ማድረስ አልቻሉም ተብሏል።
የአገር መከላከያ አባላት የሆኑትን ጨምሮ ማንነታቸውን መሠረት ተደርጎ የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ፤ በመላው አገሪቱ የትግራይ ተወላጆች የጅምላ እስር ይቁም ይላል።
ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረጉትና የትግራይ ኃይሎችን እየመሩ እንደሆነ የሚነገርላቸው ጄነራል ጻድቃን ገ/ትንሳይ በአፋር እና አማራ ክልሎች ጥቃት የከፈቱት በፌደራሉ መንግሥት ላይ ጫና ለማሳደር መሆኑን ገልጸዋል።
"ጦርነቱን የምናደርገው በሁለት ዋነኛ ምክንያቶች ነው። የመጀመሪያው በክልሉ ያለውን መዘጋት (ብሎኬጅ) ለመስበር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ያስቀመጥናቸውን ቅድም ሁኔታዎች መንግሥት እንዲቀበል ጫና ለማሳደር ነው" ብለው ነበር።
የኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሚኒስትር የሆኑት አቶ ዛዲግ አብረሃ በበኩላቸው ለቢቢሲ ሲናገሩ መንግሥት ከህወሓት አመራሮች ጋር ድርድር እንደማያደርግ ገልጸዋል።
አክለውም "አሁን በህወሓት በኩል የሚታየው ነገር ራስን አጋኖ ከማየት የመነጨ ነው። ነገር ግን መንግሥት ትዕግስቱ ሲሟጠጥ ተገቢውን እርምጃ እንደሚወስድ አቅማችንን ማየት ከፈለጋችሁ የተወሰኑ ሳምንታት መጠበቅ ይኖርባችኋል። ትዕግስታችን የተሟጠጠ ለታ እንዴት ከእያንዳንዱ ከተማና መንደር ጠራርገን እንደምናስወጣቸው ታያላችሁ። ጦርነት ከሆነ ፍላጎታቸው....ያገኙታል" ሲሉ ተናግረዋል።
የእርዳታ አቅርቦትን በተመለከተ ደግሞ መንግሥት ችግር ያለበት በቁጥር ውስን ካሏቸው የህወሓት አመራሮች ጋር እንጂ ከትግራይ ሕዝብ ጋር እንዳልሆነ ጠቅሰው "መንግሥት ወደ ክልሉ የሚገባ የሰብአዊ እርዳታን ፈጽሞ አላገደም ይልቁንም ከየትኛውም የእርዳታ ሰጪ በላይ መንግሥት አብዛኛውን ድጋፍ ለክልሉ ሕዝብ እያደረገ ነው" ብለዋል።
በትግራይ ያለው ቀውስ ከፍተኛ ሰብአዊ ኪሳራ አድርሷል። የተባበሩት መንግሥታት የህጻናት አድን ድርጅት ዩኒሴፍ ባለፈው ሳምንት አርብ ባወጣው መግለጫ ትግራይ ውስጥ ከ100 ሺ በላይ ህጻናት ከፍተኛ የምግብ እጥረት እንዳጋጠማቸውና የሞት ስጋት ውስጥ እንደሚገኙ ገልጿል። በተጨማሪም ግማሽ የሚሆኑት ነብሰ ጡርና የሚያጠቡ እናቶች ከፍተኛ የምግብ እጥረት እንዳገጠማቸው አስታውቋል።
አንዳንድ ባለሙያዎች በአጠቃላይ 400 ሺህ የሚሆኑ ዜጎች ረሃብ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ደግሞ እስከ 5.2 ሚሊየን የሚደርሱ ሰዎች ትግራይ ውስጥ አስቸኳይ የሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጿል። በተጨማሪም ወደ አፋር ክልል የተስፋፋው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን እንዳፈናቀለም ገልጿል።
ወደ ትግራይ የሚገቡ የእርዳታ መስመሮች ከአፋር በኩል ከሚወስደው መንገድ በስተቀር ተዘግተዋል። በቅርቡም በመንግሥት ደጋፊ ሚሊሻዎች የእርዳታ ምግብ ማመላለሻ መኪኖች ጥቃት እንደደረሰባቸው ተዘግቧል።
የትግራይ ኃይሎች በበኩላቸው የኢትዮጵያ መከላከያና የአማራ ኃይልን በማሸነፍ በሱዳን በኩል አዲስ የአርዳታ መሸጋገሪያ ለመክፈት ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።
በትግራይ 5.2 ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎች የሰብዓዊ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገልጿል። በቅርቡ ወደ አፋር ክልል ጦርነቱ መስፋፋቱን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከመኖሪያቸው እንዲፈናቀሉ እና ለምግብና መጠለያ ችግር ተዳርገዋል።
ባለፉት ጥቂት ቀናት በኢትዮጵያ የተከሰተውን ቀውስ ለመቆጣጠርና መፍትሄዎችን ለመፈለግ በርካታ ዲፐሎማሲያዊ ሙከራዎች እየተደረገ እንደሆነ የሚገልጹት የወርልድ ፒስ ፋውንዴሽን ዋና ኃላፊ አሌክስ ደ ዋል፤ ውይይቶቹ ግን ከመጋረጃ ጀርባ እየተከናወኑ እንደሆነ ያስረዳሉ።
ከሳሃን ምርምር ማዕከል የመጡት ማት ብራያን ደግሞ በአሁኑ ጊዜ ለችግሩ ፖለቲካዊ መፍትሄ ማግኘት ከባድ መሆኑን ይገልጻሉ።
"የትግራይ ኃይሎች ወደ ፖለቲካዊ ድርድር የሚመጡ ከሆነ በወታደራዊው ዘመቻ ያገኟቸውን ነገሮች በሙሉ ሊያጡ ይችላሉ፤ በሌላ በኩል የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መንግሥት ደግሞ ለድርድር ዝግጁ አይመስልም።"
"ይህ ጦርነት ሊያበቃ የሚችለው ትግራይ ነጻነቷን ማወጅ ስትችል አልያም ሁለቱም ወገኖች ከፍተኛ ጉዳትና ኪሳራ ከደረሰባቸው በኋላ ይመስለኛል" በማለት ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።