የ100 ዓመቱ አዛውንት በናዚ አባልነት ተጠርጥረው ፍርድ ቤት ሊቀርቡ ነው

ታትሟል

የ100 ዓመቱ ግለሰብ የናዚ አባል በነበሩ ጊዜ ለ3 ሺህ 518 ግድያዎች ተጠያቂ ናቸው ተብለው ተጠርጥረው ችሎት ፊት ሊቆሙ እንደሆነ ተሰምቷል።

ስማቸው ያልተጠቀሰው አዛውንት ጀርመን ውስጥ ነው በወንጀል ተጠርጥረው ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ የተወሰነው።

አዛውንቱ በፈረንጆቹ ከ1942 እስካ 45 ባለው ጊዜ በርሊን አቅራቢያ በሚገኘው የሳችሴንሃውሰን ካምፕ ብዙዎች እንዲገደሉ አድርገዋል ተብለው ነው የተጠረጠሩት።

አዛውንቱ በወቅቱ ሰዎች በጥይትና በመርዛማ ጭስ እንዲገደሉ አድርገዋል ተብለው ተጠርጥረዋል።

ባለፈው ማክሰኞ አቃቤ ሕግ አዛውንቱ በሚቀጥለው ጥቅምት በሚውለው ችሎት ፊት ቆመው መታደም ይችላሉ ብሏል።

አቃቤ ሕግ እንደሚለው ሰውዬው ምንም እንኳ ዕድሜያቸው የገፋ ቢሆንም በተደረገላቸው የህክምና ምርመራ መሠረት ችሎት መታደም የሚችል አቋም ላይ ነው ያሉት።

የሕግ ሰዎች ሰውዬው ቢያንስ በቀን ለሁለት ሰዓት ተኩል ፍርድ ቤት መቅረብ እንደሚችሉ አረጋግጠናል ብለዋል።

የ100 ዓመቱ አዛውንት ፍርድ ቤት ቀርበው መከራከር እንደሚችሉ ባለፈው እሁድ የዘገበው የጀርመኑ ቬልት አም ሶንታግ ጋዜጣ ነው።

ጋዜጣው አንድ ቶማስ ዋልተር የተሰኙ ጠበቃን ዋቢ አድርጎ እንደፃፈው አብዛኛዎቹ ከሳሾች ልክ እንደተከሳሽ ዕድሜያቸው የገፋ ነው።

የጀርመን መገናኛ ብዙሃን ይህን የችሎት ወሬ የናዚ ዘመን የመጨረሻው አሳሳቢ ወንጀል እያሉ እየጠሩት ነው።

በጀርመን ናዚ ዘመን ወንጀል የፈፀሙም ሆኑ ወንጀል የተፈፀመባቸው አብዛኛዎቹ ሰዎች አሁን ዕድሜያቸው እጅግ ገፍቷል።

ከ1936 እስካ 45 ባለው ጊዜ ከ200 ሺህ በላይ እሥረኞች በሳችሴንሃውሰን ካምፕ ታሥረው ነበር።

ተቃዋሚ ፖለቲከኞች፣ የጦርነት እሥረኞች እንዲሁም የተፈረደባቸው ቡድኖች ኤስኤስ በመባል በሚታወቀው የናዚ የደህንነት አደረጃጀት ሥር ተይዘው ቆይተዋል።

የሳችሴንሃውሰን ሙዚዬም እንደሚለው በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ እሥረኞች በእሥር ቤቱ ሳሉ ባጋጠማቸው ረሃብ፣ ሕመም፣ የጉልበት ብዝበዛና የማጥፋት ሥራ ምክንያት ሞተዋል።

ጀርመን ከ10 ዓመታት በፊት አንድ የናዚ ካምፕ ጠባቂ የነበረ ሰው ለጅምላ ግድያ ተባባሪ ሆኗል ስትል መፍረዷ ይታወሳል።

ምንም እንኳ ሰውዬው ይግባኝ ጠይቆ የመጨረሻ ፍርዱን ሳይሰማ ቢሞትም የውሳኔው ሕጋዊ አንድምታ ትልቅ ነው ተብሎ ነበር።

ከዚያ ቀደም ፍርድ ቤት ሰዎቹ ቀጥታ ተሳታፊ የሆኑበት ማስረጃ ማቅረብን ግዴታ ያደርግ ነበር።

ባለፈው ዓመት አንድ የ93 ዓመት የቀድሞ የናዚ ካምፕ ጠባቂ ከ5 ሺህ በላይ ለሚሆኑ እሥረኞች ግድያ ተባባሪ ነበር ተብሎ ተፈርዶበት ነበር።