ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካዊው ጠመንጃ አምራች ለአንድ ትምህርት ቤት ተኩስ ሰለባዎች 33 ሚሊዮን ዶላር ሊከፈል ነው
በአሜሪካ አንድ ትምህርት ቤት ላይ በተፈፀመ የተኩስ ጥቃት በርካቶች መገደላቸውን ተክትሎ ጥቅም ላይ የዋለውን ጠመንጃ የሠራው ኩባንያ ለተጎጂ ቤተሰቦች 33 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፍል ተወሰኖበታል።
በአሜሪካ ጥንታዊው መሣሪያ አምራች ሬሚንግተን በአውሮፓውያኑ 2012ቱ የሳንዲ ሁክ እልቂት ተብሎ በሚታወቀው የትምህርት ቤት ተኩስ ላይ ጠመንጃው በተግባር በመዋላቸው ነው ካሳ እንዲከፍል የተበየነበት።
ኩባንያው ከስሬያለሁ በሚል ለፍርድ ቤት ቢያስረዳም 33 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍል ቅጣት ተጥሎበታል።
ውሳኔው ከ26ቱ ተጠቂዎች መካከል የዘጠኙ ቤተሰቦች ላቀረቡት ክስም ምላሽ ነው፡
እያንዳንዱ ቤተሰብ 3.66 ሚሊዮን ዶላር ያገኛል ተብሏል።
ሆኖም የሬሚንግተንን የክስረት ክስ በበላይነት በሚመለከቱት የአላባማ ዳኛ ፈቃድ ላይም የተመሰረተ ነው።
ገንዘቡ ቤተሰቦቹ ከጠየቁት በእጅግ ያነሰ ነው ተብሏል፡፡
በየካቲት ወር በስህተት የመግደል ወንጀል ቅጣት ለእያንዳንዱ 225 ሚሊዮን ዶላር ይሆናል በሚል በፍርድ ቤት ተከራክረዋል።
ይህም ማለት አጠቃላይ የቅጣት አቤቱታዎች ምናልባት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
የቤተሰቦቹ ጠበቃ ጉዳዩን አስመልክቶ "ቀጣይ እርምጃዎችን እንመለከታለን" ብለዋል፡፡
ጠበቃው ጆሽ ኮስኮፍ በሰጡት መግለጫ "ክሱ የተጀመረው በአውሮፓውያኑ 2014 ሲሆን የቤተሰቦቹ ትኩረት ቀጣዩን ሳንዲ ሁክ መከላከል ላይ ያተኮረ ነበር" ብለዋል፡፡
በጠመንጃዎቹ ዕውቅናን ያተረፈው ሬሚንግተን የተመሰረተው በአውሮፓውያኑ 1816 ነው።
የሬሚንግተን ከፊል አውቶማቲክ ጠመንጃ በሳንዲ ሁክ ግድያ ላይ በመዋሉ የተጎጂዎች ቤተሰቦች ወታደራዊ መሰል መሳሪያ በጭራሽ ለሲቪል ሊሸጥ አይገባም ሲሉ በጠመንጃው አምራች ላይ ክስ መስርተዋል፡፡
ክሱ ብዙ ውጣ ውረዶች ገጥሞታል፡፡
ሬሚንግተን ጠመንጃ አምራቾች ምርቶቻቸው በወንጀል ድረጊት ጥቅም ላይ የሚውሉ ከሆነ በህግ ተጠያቂ እንዳይሆኑ እአአ በ 2005 በወጣው ህግ የተጠበቁ ናቸው ብሏል፡፡
እአአ በ 2019 ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሬሚንግተን ላይ ክሱ እንዲቀጥል ፈቀደ፡፡
ቀደም ሲል በትምህርት ቤቶች ውስጥ የጠመንጃ ወንጀሎችን የምታውቀው አሜሪካ የትምርህርት ቤቱ ተኩስ ድንጋጤን ፈጥሮ ነበር፡፡
ወንጀለኛው 20 ተማሪዎችን እና ስድስት መምህራንን ገድሏል፡፡ ቀደም ሲልም እናቱን በጥይት ገድሏል፡፡ በመጨረሻም ፖሊሶች ትምህርት ቤቱን ሲከቡ ራሱን ገደሏል፡፡
ስድስት እና ሰባት ዓመት የሆናቸው ሕጻናት ቢሞቱም ከሳንዲ ሁክ ክስተት በኋላ አዲስ ብሔራዊ የጦር መሣሪያ ቁጥጥር ሕግ አልወጣም፡፡