ኢዜማ በ28 ምርጫ ወረዳዎች ላይ ያቀረበው 'ምርጫው ይደገምልኝ' የፍርድ ቤት አቤቱታ ዛሬ መታየት ይጀምራል

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Citizens for Social Justice
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ፣ በምህጻሩ ኢዜማ ሰኔ 14፤ በተካሄደው ምርጫ በሃያ ስምንት ምርጫ ወረዳዎች የምርጫው ይደገምልኝ ጥያቄ አቤቱታ ዛሬ በጠቅላይ ፍርድ ቤት መታየት ይጀምራል፡፡
ኢዜማ በነዚህ ምርጫ ወረዳዎች የተፈጸሙ ግድፈቶች አሉ በሚል ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት መውሰዱን በፌስቡክ ገጹ ላይ ይፋ አድርጓል፡፡
ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤቱታ ያስገባው ኢዜማ፤ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት የወሰድኩት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያቀርብኩለትን ቅሬታዎች እንዲሁም ማስረጃዎችን ሳይገመግም ውሳኔ ስላስተላለፈብኝ ነው ብሏል፡፡
ኢዜማ በፌስቡክ ገጹ እንዳለው ሰኔ 14 በተደረገው አገራዊ ምርጫ ከድምጽ አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ከቀበሌ እስከ ክልል ባሉ የገዢው ፓርቲ አመራሮች፣ ከቀበሌ ሚሊሻ እስከ ክልል ልዩ ኃይል ድረስ ባሉ የጸጥታ አስከባሪዎች፣ ምርጫ አስፈጻሚዎችና ማንነታቸው ባልታወቁ ግለሰቦች አማካኝነት ምርጫው ሲስተጓጎል ነበር ሲል ከሷል፡፡ ይህም በምርጫው ውጤት ላይ ተጽእኖ አሳድሯል ብሏል፡፡
ለዚህም በቂ የሆነ የሰው፣ የሰነድ የቪዲዮና የምሥል ማስረጃዎችን ማጠናቀረውን በፌስ ቡክ ገጹ አውስቷል፡፡
ኢዜማ ለኢፌድሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ትናንት ያስገባው አቤቱታ ጥሰት ተፈጽሞባቸዋል ባላቸው 28 የምርጫ ወረዳዎች ምርጫው በድጋሚ እንዲካሄድ ፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲያተላልፍለት በመጠየቅ ነው፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት 2ኛ የምርጫ ጉዳዮች ችሎት ዛሬ ሐምሌ 15 ከጠዋት ጀምሮ የቀረበለትን አቤቱታ መመልከት ይጀምራል፡፡








