በናይጄሪያ ታግተው የነበሩ 100 እናቶችና ሕጻናት ተለቀቁ

አሸዋ ውስጥ የቀረ ነጠላ ጫማ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

በሰሜን-ምዕራብ ናይጄሪያ የሚገኙ ባለሥልጣናት በሽፍቶች ታግተው የቆዩ 100 ሕፃናትን እና የሚያጠቡ እናቶችን አስለቀቁ።

ታጋቾቹ ሰኔ 8 ቀን በዛምፋራ ግዛት የታፈኑ ሲሆኑ በወቅቱ አራት ሰዎች ተገድለው ነበር።

የዛምፋራ ግዛት መንግሥት ምንም አይነት ገንዘብ ሳይከፍል ታጋቾችን ማስለቀቁን ቢገልጽም እንዴት እንዳስለቀቋቸው ግን ተጨማሪ መረጃ አልሰጠም።

ነጻ የወጡት ታጋቾችም ወደ ቤታቸው ከመመለሳቸው በፊት ሕክምና እና ስለጉዳዩ ማብራሪያ ይሰጣቸዋል ተብሏል።

ከቅርብ ወራት ወዲህ በግዛቱ በርካታ የእገታ ድርጊቶች ተፈጽመዋል።

ከታኅሳስ ወር ጀምሮ ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች ታፍነው ተወስደው ነበር። ከታገቱት መካከል በርካቶቹ በኋላ ላይ ነጻ ወጥተዋል።

እነርሱን ለማስለቀቅም ክፍያዎች መፈጸማቸው የተዘገበ ሲሆን የተወሰኑት ግን ተገድለዋል።

የመንግሥት ባለሥልጣናቱ ድርጊቶቹ የሚፈፀሙት በሽፍታዎች እንደሆነ ይገልጻሉ።

ይህ ሽፍታ የሚለው ቃል በሰፊው ለተለያዩ ቡድኖች የሚውል ቃል ሲሆን አጋቾች፣ ታጣቂ ዘራፊዎች፣ ከብት ዘራፊዎች እና በክልሉ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሌሎች ታጣቂ ኃይሎች እገታውን የሚፈፅሙት በአብዛኛው ገንዘብ ለመጠየቅ ሲሉ ነው።

እ.አ.አ. በ2014 የቦኮ ሃራም እስላማዊ ታጣቂዎች ከቺቦክ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 276 ሴት ተማሪዎችን አፍነው ከወሰዱበት ጊዜ አንስቶ በርካታ የታጠቁ ቡድኖች ተማሪዎችን በጅምላ ጠለፋ ማድረግ ጀምረዋል።

ፕሬዝዳንት ሙሃመዱ ቡሃሪ በዛምፋራ እና አጎራባች በሆኑት የካዱና እና ካትሲና ግዛቶች ወንጀለኞችን እንዲያጠፉ ለወታደሮቻቸው መመሪያ ሰጥተው ነበር።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ በአንድ የወንጀል ቡድን ላይ በተደረገ ወረራ አንድ የናይጄሪያ አየር ኃይል አውሮፕላን በዛምራ እና በካዱና ግዛቶች ድንበር ላይ ተመትቶ ተጥሏል። አብራሪው ከአውሮፕላኑ በመውረድ እና በመሸሹ ራሱን ማትረፍ ችሏል።