የናይጄሪያ ታጣቂዎች ነርሶችና ጨቅላ ሕፃናትን አግተው መውሰዳቸው ተገለጸ

የናይጄሪያ ካርታ
ታትሟል

በሰሜን ምዕራብ ናይጄሪያ ውስጥ ታጣቂዎች ከአንድ ሆስፒታል ቢያንስ ስምንት ሰዎችን አፍነው ወስደዋል ሲል ፖሊስ አስታወቀ።

ጥቃቱ እሁድ ማለዳ በዛሪያ በሚገኘው ብሔራዊ የሳንባ በሽታ እና የሥጋ ደዌ ማዕከል ውስጥ ነው የተፈጸመው።

ሪፖርቶች እንደሚሉት በቡድኑ የተወሰዱት ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ሲሆን ነርሶች እና ሕፃናትን ያካትታል።

ናይጄሪያ ውስጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ገንዘብ ለማግኘት ሲባል ከትምህርት ቤቶች እና ከዩኒቨርሲቲዎች የሚደረጉ እገታዎች እየተበራከቱ ነው።

በተጨማሪም ፖሊስ በአካባቢው "ሽፍቶች" ተብለው የሚታወቁ የወንጀል ቡድኖች ናቸው ያላቸው ታጣቂዎች በከተማዋ በሚገኘው የፖሊስ ጣቢያ ላይ ተኩስ ከፍተዋል ብሏል።

በፖሊስ ጣቢው የተኩስ ልውውጡ ሲካሄድ ሌላ ቡድን በሆስፒታሉ ላይ ጥቃት ሰንዝሯል።

የአካባቢው ነዋሪ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደተናገሩት "በፖሊስ ጣቢያው ላይ የተፈጸመው ጥቃት ትኩረት ለማስቀየር የተደረገ ሲሆን ሌላ ቡድን ደግሞ የጤና ጣቢያ ሠራተኞች ማደሪያን አጥቅቷል።"

ቡድኑ ከታጋቾች ጋር በመሆን በአቅራቢያው ወደሚገኘው ጫካ አምልጧል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የሆስፒታሉ ሠራተኛ ለቢቢሲ የሃውሳ ቋንቋ አገልግሎት እንደተናገሩት፤ ታጣቂዎቹ ከሦስት ዓመት በታች የሆኑ ሦስት ሕፃናትን እና ታዳጊዎችን ጨምሮ ቢያንስ 12 ሰዎችን አፍነው ወስደዋል።

የአካባቢው የመንግሥት ባለሥልጣን እንደተናገሩት፤ ወታደሮች ታጋቾችን ለማግኘት ጥረታቸውን እያጠናከሩ ነው።

በተመሳሳይ እሁድ ለሊት ከቤተል ባፕቲስት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ታግተው ተወስደዋል።

አንድ ልጃቸው የታገተባቸው ቤተሰብ 140 ተማሪዎች መወሰዳቸውን ለቢቢሲ ተናገረዋል።

ትምህርት ቤቱ ሰዎች ከታፈኑበት የጤና ተቋም በቅርብ ርቀት ላይ እንደሚገኝ ታውቋል።

የታፈኑት ተማሪዎች ቁጥር በእርግጠኝነት ባይታወቅም የአካባቢው ነዋሪዎች እና መሪዎች ቁጥሩ ከመቶ በላይ ነው ይላሉ።

የ15 ዓመት ልጃቸው የታፈነችባቸው አንዲት እናት እንዳሉት፤ ታጣቂዎቹ እሁድ ከእኩለ ለሊት በኋላ የትምህርት ቤቱን የጀርባ አጥር ሰብረው ገብተዋል።

ታጣቂዎቹ በሞተር ሳይክል መምጣታቸውን እና ቁጥራቸው 60 እንደሚደርስ ገልጸዋል።

በአገሪቱ ውስጥ እገታዎች እየጨመሩ ነው። ከታኅሣሥ ወዲህ ብቻ በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ታፍነው ተወስደዋል። ከእነዚህ መካለከል ዘጠኙ ተገድለዋል።

ባለፈው የካቲት ወደ 300 የሚጠጉ ተማሪዎች ዛምፋራ ግዛት ከሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት ታፍነው ተወስደዋል።

ባለሥልጣናት እንደገለጹት፤ በቅርቡ በሰሜን ምዕራብ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ላይ ጥቃቶች የተፈጸሙት በዋነኝነት ለገንዘብ ሲባል ነው።

እአአ በ2014 በቦርኖ ግዛት በቦኮሃራም እስላማዊ ታጣቂዎች ከቺቦክ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 276 ሴት ልጆች ታፍነው ከተወሰዱ ወዲህ የታጠቁ ቡድኖች ተማሪዎችን በጅምላ ማፈን ጀምረዋል።