በሙስና የተጠረጠሩ ሩሲያዊ ፖሊሶች ቤት ውስጥ የወርቅ ሽንት ቤት ተገኘ

የፎቶው ባለመብት, sledcom.ru
የሩሲያ መርማሪዎች በሙስና የተጠረጠሩ የትራፊክ ፖሊሶች ቤት ውስጥ የወርቅ ሸንት ቤትና ሌሎች በቅንጦት የተሞሉ ቁሳቁሶችን እንዳገኙ አስታውቀዋል።
መርማሪዎች ቅንጡ የሆነው ቤት በድንገት ባደረጉት ፍተሻም በሙስና የተጠረጠሩ የትራፊክ ፖሊሶችን ቡድን ይዘናል ብለዋል።
የመርማሪው ኮሚቴ ቪዲዮ እንደሚያሳየው ቅንጡ የሆነው ቤት በጣም ትልቅ፣ ማዕድ ቤቱም በወርቅ የተንቆጠቆጠና ለየት ባሉ ቁሶችም የተሞላ ነው።
የደቡብ ስታቭሮፖል ግዛት የትራፊክ ፖሊስ ኃላፊ ኮሎኔል አሌክሴ ሳፎኖቭን ጨምሮ ስድስት የትራፊክ ፖሊሶች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
የትራፊክ ፖሊሶቹ የንግድ እቃዎችን ለሚያመላልሱ አሽከርካሪዎች ሃሰተኛ ፈቃድ ሲሰጡ ነበር በምላሹም ጉቦ ተቀብለዋል ተብሏል።
የትራፊክ ፖሊሶቹ በሚሰጧቸው ፈቃድ አማካኝነት አሽከርካሪዎቹ ያልተፈቀዱ የእህል ጭነቶች እና የግንባታ ቁሳቁሶችን ይዘው በፖሊስ ኬላዎች ውስጥ እንደፈለጉ እንዲያልፉ ማስቻሉም ተገልጿል።
ተጠርጣሪዎቹ በተከሰሱበት ወንጀል ላይ እስካሁን የሰጡት አስተያየት የለም ፡፡
በመላው የሩሲያ ሰሜን ካውካሰስ የፖሊስ ኃይሎች በፀረ-ሙስና ዘመቻው ተሳትፈዋል።
የትራፊክ ፖሊስ ጽ / ቤቶችን ጨምሮ ወደ 80 ያህል ስፍራዎች ፍተሻ ተካሂዶ ከፍተኛ ገንዘብ እና የቅንጦት መኪናዎችን በቁጥጥር ስር መዋሉንም ኮሚቴው አስታውቋል።

የፎቶው ባለመብት, sledcom.ru

የፎቶው ባለመብት, sledcom.ru

የፎቶው ባለመብት, sledcom.ru
ከአሜሪካው ኤፍ.ቢ.አይ (FBI) ምሳሌነት የተዋቀረው የሩሲያ መንግሥት አካል የሆነው "ኤስ.ኬ" እንዳስታወቀው የትራፊክ ፖሊስ ኃላፊው ቡድን ከ 19 ሚሊዮን በላይ ሩብልስ ወይም 255 ሺህ ዶላር በአመታት ውስጥ በጉቦ ማግኘት ችሏል።
ኃላፊው ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ እስከ 15 ዓመት እስር ሊፈረድባቸው እንደሚችልም ተነግሯል። የቀድሞው የትራፊክ ፖሊስ ኃላፊ አሌክሳንደር አርዛኑኪን ከታሰሩት መካከል አንዱ ናቸው።
በክሬምሊን የተባበሩት የሩሲያ ፓርቲ የፓርላማ አባል የሆኑት አሌክሳንደር ኪንሽቴይን በበኩላቸው በክልሉ ከ35 በላይ የትራፊክ ፖሊሶች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።
በቴሌግራም በላኩት መልዕልት "በመሠረቱ ፣ በእውነቱ የሚገርም የማፊያ ቡድን በስታቭሮፖል ከሁሉም ነገር እያተረፈ ነበር። ከጥቁር ገበያ፣ የታርጋ ፍቃድ፣ ካርጎ እቃዎች፣ የአሸዋ ምርቶችና ሌሎችም ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ገንዘብ እያተረፉ ነበር" ብለዋል።












