ጣና ሐይቅ፡ 13 ሰዎችን አሳፍራ ከተሰወረችው ጀልባ የ7ቱ ሰዎች አስክሬን መገኘቱ ተገለጸ

ጣና ሐይቅ

የፎቶው ባለመብት, EDUARDO SOTERAS

ታትሟል

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምስራቅ ደንቢያ ወረዳ ወደ 13 የሚጠገቡ ሰዎችን አሳፍራ በጣና ኃይቅ ላይ በተሰወረችው ጀልባ ተሳፍረው ከነበሩ የ7 ሰዎች አስክሬን መገኘቱ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የወረዳውን ፖሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ቸርነት አስማረን ጠቅሶ እንደዘገበው በአደጋው ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች የተገኙት ላለፉት ሁለት ቀናት በጀልባና በዋናተኞች በተደረገ አድካሚ ፍለጋ በኋላ ነው።

አስከሬኖቹ ዛሬ ንጋት በጎርጎራና አዲስጌ ድንጌ በተባለ የገጠር ቀበሌ መካከል በሐይቁ ላይ በማዕበል ተገፍተው ተንሳፈው መገኘታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ኮማንደር ቸርነት የቀሪዎቹን ስድስት ሰዎች አስከሬን ለማግኘት ፍለጋው ተጠናክሮ መቀጠሉን ለዜና ወኪሉ ተናግረዋል።

የአደጋውን ምክንያት የሚያጣራ ግብረ ኃይልም ተቋቁሞ ምርመራ ተጀምሯል ተብሏል፡፡

ይህች አነስተኛ ጀልባ ጉዞ የጀመረችው ሐምሌ 9፣ 2013 ዓ.ም ሌሊት ላይ የነበረ ሲሆን፤ አዲሰጌ ድንጌ ተብሎ ከሚጠራ ቀበሌ አባን ላይ ጎጥ ወደ ጎርጎራ ወደብ ጉዞ ላይ ሳለች ነበር የተሰወረችው።

ከመነሻው እስከ መዳረሻው ያለው የውሃ ጉዞ የ15 ኪሎ ሜትር ርቀት አለው ተብሏል።

ፖሊስ ከቤተሰቦቻቸው አገኘሁት ባለው መረጃ መንገደኞቹ ሌሊት ድንች ጭነው በጀልባ የተሳፈሩ ሲሆን መዳረሻቸው ጎርጎራ ወደብ ነበር።

ይሁን እንጅ በሥፍራው ሳይደርሱ ቀርተዋል።

የመንገደኞቹ ቁጥር ከ10-13 ያህል ይሆናል የተባለ ሲሆን የአብዛኞቹን ማንነትና የስም ዝርዝራቸውን ማግኘት ተችሏል ተብሏል።