የግድቡን ጉዳይ የተመለከተው የፀጥታው ምክር ቤት ማን ነው? ኃላፊነቶቹስ ምንድን ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የምትገነባውን ግዙፍ ግድብ ውሃ መሙላት እንድታቆም ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ ቱኒዚያ ማቅረቧን የዲፕሎማቲክ ምንጮች አስታውቀው ነበር፡፡
ግድቡ በአገራቱ መካከል አለመግባባትን የፈጠረ ሲሆን፤ ግብፅ እና ሱዳን፤ ኢትዮጵያ ግድቡን ከመሙላቷ በፊት አስገዳጅ የሆነ ስምምነት እንዲደረስ ጠይቀዋል። የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ጉዳዩን እንዲያየው ጥሪ አቅርበውም ጉዳዩ በምክር ቤቱ ታይቷል፡፡
ኤኤፍፒ ያገኘው ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ ግብፅ፣ ኢትዮጵያ እና ሱዳን የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበር እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ በጋራ በሚገኙበት ድርድሩን እንደገና እንዲጀምሩ ጥሪ ያቀርባል፡፡ በግድቡ ሙሌት እና አሠራር ላይ አስገዳጅ የሆነ ስምምነት በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ እንዲደረስም ይላል፡፡
የውሳኔ ሐሳቡ አክሎም ስምምነቱ "በታችኛው የተፋሰሱ አገራት የውሃ ደኅንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳይደርስ በመከላከል ኢትዮጵያ ከግድቡ ኃይል የማመንጨት አቅሟን ማረጋገጥ አለበት" ይላል።
ሦስቱ አገራት ማንኛውንም መግለጫ ከመስጠት ወይም የድርድር ሂደቱን አደጋ ላይ ከሚጥል ማንኛውም አይነት እርምጃ እንዲቆጠቡ ያሳስባል። ኢትዮጵያም በተናጠል ግድቡን እንዳትሞላ ይጠይቃል።
ኢትዮጵያ በበኩሏ ግድቡን መሙላት መጀመሯን ለታችኛዎቹ የተፋሰሱ አገራት ማሳወቋን ገልጻለች።
ኢትዮጵያ እአአ በ2015 በሦስቱ አገራት መካከል በተደረሰው ስምምነት መሠረት፤ ግብፅ እና ሱዳን ለዝግጅት እንዲያመቻቸው ሲባል የግድቡን ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጀመሯን በይፋዊ ደብዳቤ እንዳስታወቀቻቸው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የተደራዳሪ ከሚቴ አባል ፕ/ር ይልማ ስለሺ መናገራቸውን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘግቧል፡፡
ባለፉት አሥር ዓመታት መሠረታዊ መረጃ ለማግኘት የግንባታ ቦታው ድረስ ሄደው በማየት፣ ከውሃ ባለሙያዎች፣ ከፖሊቲካኞች እንዲሁም ከዲፕሎማቶች ጋር ሲወያዩ እንደነበር ፕ/ር ይልማ ይናገራሉ።
ኢትዮጵያ በይፋዊ ደብዳቤ የሰጠችው መረጃ ይህን መርህ የተመርኮዘ እንደሆነ ገልጸው፤ ይህም የመረጃ ልውውጥ አንዱ አካል ነው ሲሉ አብራርተዋል።
አገራቱም ይህንን በመገንዘብ በእነሱ በኩል የሚያስተካክሏቸውን ጉዳዮች ሲያስተካክሉ ነበር ያሉት ፕ/ር ይልማ፤ "አገራቱ በስምምነታቸው መሠረት ግድቡ ሐምሌና ነሐሴ ላይ እንደሚሞላ ያውቁታል። ነገር ግን ማረጋገጫ እንዲሆናቸው ተነግሯቸዋል" ብለዋል፡፡
ታላቁ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን ውዝግብ ውስጥ ከገቡ ወደ አሥር ዓመታት ተቆጥረዋል።
ሱዳን እና ግብፅ በጉዳዩ ላይ የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት እንዲመክር ጠርተው ነበር። ምክር ቤቱም በጉዳዩ ላይ ውይይት አካሂዷል። ለመሆኑ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ማን ነው? ኃላፊነቶቹስ ምንድን ናቸው?
የፀጥታው ምክር ቤት
የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ከተባበሩት መንግሥታት ዋና ዋና አካላት አንዱ ነው።
ምክር ቤቱ ዓለም አቀፍ ሠላምና ደኅንነትን የመጠበቅ ቀዳሚ ኃላፊነት አለበት ይላል በድረ ገጹ የሰፈረው መረጃ፡፡ 15 አባላት ያሉት ሲሆን እያንዳንዱ አባል አንድ ድምጽ አለው፡፡
በተባበሩት መንግሥታት ስምምነት መሠረት ሁሉም አባል አገራት የምክር ቤቱን ውሳኔ የማክበር ግዴታ አለባቸው፡፡
የፀጥታው ምክር ቤት ሠላምን የሚያናጋ አደጋ ወይም ስጋት መኖሩን ይመረምራል።
ያልተግባቡ ወገኖች በሠላማዊ መንገድ ችግሮቻቸውን እንዲፈቱ ጥሪ የሚያደርግ ሲሆን፤ የማስተካከያ ዘዴዎችን ወይም የመፍትሔ ሐሳቦችን ያቀርባል፡፡
"ምክር ቤቱ አንዳንድ ጊዜም ዓለም አቀፍ ሠላም እና ፀጥታን ለማስጠበቅ ወይም ወደነበረበት ለመመለስ ማዕቀቦችን መጣል ወይም አልፎ የኃይል እርምጃዎችን እንዲወሰድ ሥልጣን ሊሰጥ ይችላል" ይላል የድረጅቱ ድረ ገጽ፡፡
በአባል አገራት ላይ አስገዳጅ የውሳኔ ሐሳቦችን የማውጣት ብቸኛው ሥልጣን ያለው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካል ነው፡፡
እአአ ጥር 17/1946 የመጀመሪያውን ስብሰባውን ያካሄደ ሲሆን፤ በቀጣዮቹ አሥርት ዓመታት ውስጥ በአሜሪካ እና በሶቪዬት ሕብረት እና በአጋሮቻቸው መካከል በቀዝቃዛው ጦርነት ምክንያት ደካማ ሆኖ ቆይቷል።
አባላቱ እነማን ናቸው?
በፀጥታው ምክር ቤት አምስት አገራት በቋሚነት ይወከላሉ፡፡ አገራቱ ምክር ቤቱ ሲመሠረት የበላይነቱን የያዘውን የድኅረ ጦርነት የኃይል አወቃቀር ያንጸባርቃሉ፡፡
ልዩ መብት ያላቸው እነዚህ አገራት ከ10 ተለዋጭ አባል አገራት ጎን ሆነው ይሠራሉ፡፡ ቋሚ የሆኑት እና ያልሆኑትም አገራት በዙር የምክር ቤቱን ፕሬዝዳንትነት ለአንድ ወር ይይዛሉ፡፡
ተለዋጭ አባል አገራት ሁሉንም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባላትን በሚወክለው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ አባላት ለሁለት ዓመት የሥራ ዘመን ይመረጣሉ፡፡
አላማው ተለዋጭ አባል አገራትን ከተለያዩ ክልሎች በመምረጥ ክልላዊ ሚዛንን ለመጠበቅ ነው፡፡
አገራት ለምክር ቤቱ አባልነት በከፍተኛ ደረጃ ይወዳደራሉ። ተያይዞ ከሚመጣው ክብር ወይም ብሔራዊ ፋይዳ አንጻር ነው ፉክክሩ። አንዳንድ አገራት እጩነታቸውን ከዓመታት በፊት አስታውቀው ድምጽ ለማግኘት ይሠራሉ፡፡
አምስት ቋሚ የምክር ቤቱ አባላት አሜሪካ፣ ቻይና ፣ ሩሲያ፣ ፈረንሳይ እና ዩናይትድ ኪንግደም ናቸው።
ተለዋጭ አባላት ደግሞ ኢስቶኒያ፣ ሕንድ፣ አየርላንድ፣ ኬንያ፣ ሜክሲኮ፣ ኒጀር፣ ኖርዌይ፣ ሴንት ቪንሰንት እና ግሬናዲንስ፣ ቱኒዚያ እና ቬትናም ናቸው።
ፈረንሳይ ለአንድ ወር የሚቆየው የወቅቱ የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ናት።
ውሳኔ አሰጣጡ ምን ይመስላል?
ረቂቅ የውሳኔ ሐሳቦች በአንድ ወይም በብዙ የምክር ቤቱ አባላት ተቀርጸው በግል ወደ ሌሎች ይሰራጫሉ፡፡
ረቂቆቹ "ምክክር" ተብሎ በሚጠራው ሂደት ድርድር ሊደረግባቸው ወይም ሊቀየሩ ይችላሉ፡፡ ሁሉም አባላት ከተስማሙ ውሳኔው በመደበኛነት ለምክር ቤቱ ይቀርባል፡፡
እያንዳንዱ አባል አንድ ድምጽ አለው፡፡ ምክር ቤቱ "ተጨባጭ" ብሎ በሚጠራቸው ጉዳዮች ላይ ውሳኔዎች ከመደረሳቸው በፊት በአብላጫ ድምጽ ዘጠኝ ድምጾች ያስፈልጋሉ፡፡
አንድ ጉዳይ ተጨባጭ ነው ወይስ አይደለም የሚለው በራሱ አከራካሪ ጉዳይ ነው፡፡
ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ምንድን ነው?
ቋሚ አባላት ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት አላቸው፡፡ ከመካከላቸው አንዱ ውሳኔውን የሚቃወም ከሆነ ሊጸድቅ አይችልም ማለት ነው፡፡ አንድ ቋሚ አባል ድምጹን ካልሰጠ ግን ውሳኔ ሊተላለፍ ይችላል፡፡
የፀጥታው ምክር ቤት የትጥቅ ግጭት መከላከልን ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ ነው። ውዝግብ አንዴ ከተነሳ ግን የመጀመሪያው አላማው ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ መፈለግ ነው፡፡
ግጭቱ ከቀጠለ ምክር ቤቱ የተኩስ አቁም እንዲኖር መሥራት እና የሠላም አስከባሪዎችን ማሰማራት ይችላል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ማዕቀቦችን እንዲጥል ማዘዝ ይችላል። እንደ መጨረሻ አማራጭም ጥቃት ፈጻሚዎች ላይ ወታደራዊ እርምጃ ሊወስድ ይችላል፡፡
ባለፉት አሥር ዓመታት አሜሪካ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብቷን በተለይም እስራኤል እና ፍልስጤምን በሚመለከቱ ውሳኔዎች ላይ ነው የተጠቀመቸው፡፡
ሩሲያ እና ቻይናም እንዲሁ ብዙውን ጊዜ የአሜሪካን ሐሳቦች ለማገድ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብታቸውን ይጠቀማሉ፡፡ በቅርቡ ሩሲያ በሶሪያ ውስጥ ስላለው ግጭት ውሳኔዎች ላይ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብቷ በተደጋጋሚ ትጠቀም ነበር፡፡
የአባላትን ቁጥር ለማሳደግ ምን እየተሠራ ነው?
የቋሚ አባላቱ አቋም ከምክር ቤቱ የመጀመሪያ ስብሰባ ወዲህ ያልተለወጠ ሲሆን፤ የፀጥታው ምክር ቤት ውህደት የተባበሩት መንግሥታት አጀንዳን ከፍ አድርጎታል፡፡
ለውጥ ለመፍጠር በርካታ መሰናክሎች ገጥመዋል። ሕንድ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባል የመሆን ፍላጎቷን አሜሪካ እንደደገፈች ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ መግለጻቸው ለለውጥ ፍላጎት ስለመኖሩ ማሳያ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
ጂ 4 በመባል የሚታወቁት ሕንድ፣ ጀርመን፣ ጃፓን እና ብራዚል እንዲሁም የአፍሪካ ሕብረት ቋሚ አባልነትን ለማግኘት ለረዥም ጊዜ ከተመኙ መካከል ናቸው፡፡
በዚህ ጉዳይ መግባባት ላይ አልተደረሰም።












