አበበች ጎበና፡ የብዙዎች እናት በልጆቻቸው አንደበት

ታትሟል

አበበች ጎበና ኢትዮጵያ ውስጥ ቀደምት የተባለውንና ሕጻናት ክብካቤና ልማት ማኅበር (አጎሕልማ) የተሰኘ ወላጅ አልባዎች ሕፃናት ማሳደጊያ መስራች ናቸው።

መነሻቸው ወሎ የሚገኘው የግሸን ማርያም ቤተ ክርስቲያንን ለመሳለም ሐይማኖታዊ ጉዞ ባደረጉበት ወቅት ነው።

ቦታው በረሃብ ተጠቅቶ የነበረ ሲሆን ከጉዟቸው ሲመለሱም አንድ ሕፃን ከሞተች እናቱ አጠገብ ተኝቶ ያያሉ።

ልጁን አንስተው ወደ ቤታቸው ወሰዱት። በዚህም አላበቃም ከሞተ አባቱ አጠገብ ተኝቶ ያገኙትንም ሁለተኛ ሕጻን እንዲሁ ወደ ቤታቸው ወሰዱ።

የልጆቹ ቁጥር ቀስ በቀስ ተመነደገ። በአንድ ዓመት ውስጥም 21 ወላጅ አልባ ህፃናትን ለማሳደግ ወደቤታቸው ያመጡት አበበች ጎበና ፍቅርና ደግነታቸውም ለሦስት አስርት አመታት በላይ አብሯቸው ቀጥሏል።

የአበበች ጎበና'እዳዬ' ልጆች

ጸሐይ ቱፋ ከእዳዬ ልጆች አንደኛዋ ናት።

ሲገናኙ አሁን የነበረው ድርጅት አልነበርም። ሃሳቡም የነበረ አይመስልም።

"ብቻቸውን ስለነበሩ ከእሳቸው ጋር እንድሆን ነው የተሰጠሁት" ትላለች።

አብራቸው ስትኖር ከልጆች ጋር ጥልቅ ግንኙነት እንደነበራቸው ታዝባለች። የሁሉንም ስሜት፣ ጉዳት፣ ፍቅር እና ሃዘን እንደሚረዱ ጭምር።

"ጥንካሬ፣ መከራን ማለፍ፣ ምንም የህይወት ፈተና ቢኖርም ማሸነፍ እና ግበረገብን" ከእሳቸው መማሯን ስትናገር በልበ ሙሉነት ነው።

ከመደበኛ ትምህርት ጎን ለጎን በህትመት እና ማስታወቂያ ሰልጥና በሙያዋ እሳቸው ጋር ስትሠራ ቆይታለች።

በኋላም ከድርጅቱ ወጥታ በግል መሥራት ጀምራለች።

ኮቪድ መጥቶ ነገሮችን ከመቀያየሩ በፊት የእዳዬ ልጆች ተሰባስበው እየሄዱ ይጠይቋቸው ነበር።

ቫይረሱ ኢትዮጵያ መግባቱ ከተነገረ በኋላ ግን ለጤንነታቸው ሲባል የውጭ ሰው እንዳይጎበኛቸው ተከለከለ።

እዳዬ በኮሮና ተይዘው ከአንድ ወር በፊት ሐኪም ቤት እንደገቡ ጸሐይ ሄዳ እንዳየቻቸው ሃዘን በተጫነው ድምጽ ተናግራለች።

ጠንካራ፣ ቀን ከለሊት የሚሠሩ ነበሩ የምትላቸው እናቷን ማለፍ የሰማችው ከእሀቶቿ መሆኑን ትገልጻለች። "ዛሬ እናታችን ሞተዋል [እያለቀሰች]" ነበር።

ተመሳሳይ ስሜት ከእህቶቿ አንዷ በሆነችው ራሔል ብርሃኑም ይነበባል። እሷም ሌላኛው የወ/ሮ አበበች ልጅ ናት። ኧረ ከቀዳሚዎቹም ልጆቻቸው መካከል ናት።

"አመጣጤን ብዙም አላስታውስም" የምትለው ራሔል በመቀጠልም ". . . እንደ እናት ነበር የሚንከባከቡኝ" ትላለች።

ከእዳዬ ጋር ብዙ ችግር አሳልፈዋል።

ደጋግ ጊዜዎቹ ግን የትየለሌ ናቸው። ትምህርት አስተምረዋቸዋል። 18 ዓመት እስኪሞላቸውም እሳቸው ዘንድ ይኖሩ ነበር።

እሳቸው ባይኖሩ ህይወት ምን እንደሚመስል ስትጠየቅ ምላሿ አጭር ነው- "ማሰብ ይቸግራል።"

"ከእናትም እናቴ ናቸው። እናት እና አባት በማላውቅበት ጊዜ ነው ያገኙኝ" ትላለች።

የእዳዬ ልጆች ለቁም ነገር በቅተዋል።

በሁለት ደጋግ ሰዎች እጅ ማደግ ምንኛ መታደል ነው?

በንግግሯ ሁሉ አባቴ ዶ/ር ካርል እና እናቴ እዳዬ፣ አበበች ጎበና፣ በተደጋጋሚ የሚደመጡ ናቸው።

ከእዳዬ ጋር የተዋወቁት የሰዎች ለሰዎች መሥራች በሆኑት ዶ/ር ካርል ሄንዝ በም በኩል ነበር።

ጊዜው በሰሜን ኢትዮጵያ በተከሰተው በድርቅ ምክንያት ከመኖሪያ ቀዬአቸው የተፈናቅሉበት ነበር።

ወለጋ አቅንተው መቱ ሰፈሩ።

"አካባቢው እናቶች ከልጆቻቸው ጡት እየነጠቁ እኛን እያጠቡ. . . እንደራሳቸው ልጆች ነበር የሚያሰድጉን" ትላለች።

አባት እና እናት ዶ/ር ካርል ሄንዝ በም እና እዳዬ ወይንም አበበች ጎበና ሲሆኑ ልጅ ደግሞ አትሌት አለም አሸብር ናት።

የአካባቢው ነዋሪ በሚቻለው ሁሉ ሲረዳቸው ቆየ። ካርል ሄንዝ በም ወደ አካባቢው ለበጎ ሥራ ሲመጡ ህብረተሰቡ ካስረከባቸው ልጆች መካከል አንዷ ለመሆን በቃች።

በኋላም "ወንድም እና እህቶቼ" ከምትላቸው ሌሎች ልጆች ጋር መቱ በሚገኘው አብዲ ቦሩ የህጻናት ማሳደጊያ ገባች።

አባትና ልጅ፣ ካርልና አለም ጥሩ ይግባቡ ነበር።

አንድ ክረምት አባት ልጁን ለእረፍትም ለትምህርትም ወደ ሌላ ቦታ ሊወስዳት ወሰነ። አለምም ከአባቷ 'አዲስ አበባ እንሄዳለን ተዘጋጂ' የሚል መልዕክት ደረሳት።

"'አንዲት ጀግና ኢትዮጵያዊት እናት አለች። አዲስ አበባ ወስጄ ላሳይሸ። ልጄ እሷ ጋር እንድትማር እፈልጋለሁ' ብለው ወሰዱኝ" ስትል ታስታውሳለች።

'እንዳንቺ ማናጀር፣ መሐንዲስ አድርጊልኝ' ብለው ነበር ክረምቱን አዲስ አበባ እንድታሳልፍ ለእዳዬ ያስረከቧት።

በዝናባማዋ አዲስ አበባ አስደሳች የክረምት ወራትን ከእዳዬ ጋር አሳለፈች።

"መጨረሻ ላይ ሁለት አማራጭ ነበረኝ። አብዲ ቦሩ ወንድሞቼ ጋር መመለስ ወይንም ከእዳዬ ጋር መቆየት። እኔ ደሞ እዳዬ በጣም ስለምወዳቸው ሥራቸው ያስደንቃል። ለሊት ተነስተው ጸሎት አድርገው ነው። ሐይማኖታቸው ላይ ጠንካራ ናቸው። ጥበባቸው አጓጓኝና እዚህ እናቴ ጋር ብኖር አልኩኝ። የተለየ ነገር አላቸው።"

"እዳዬ 'የት ይሻልሻል ሲሉኝ?' 'ከእርስዎ ጋር እሆናለሁ አልኳቸው።' በዚያ ምክንያት ከእሳቸው ጋር ቀረሁ።"

አዲስ ኑሮ፣ አዲስ ምዕራፍ አዲስ አበባ ላይ ተጀመረ።

ምንም ሳይጎድልባት 'እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ማንም የማያገኘውን እያገኘች' ማደጓን ትናገራለች።

ከእዳዬ 'ፈሪሃ እግዚአብሔር፣ አንድነት፣ የሃገር ፍቅር፣ በራስ መተማመን' እንደተማረች ደጋግማ ትገልጻለች።

በቀን ሦስቴ የጸሎት ጊዜ አላቸው።

"'ሃገራችንን መሃሏን ገነት ዳሯን እሳት አድርገህ ጠብቅ' እንላለን" የምትለው አለም "'ህዝባችንን፣ ሃገራችንን ሠላም፤ እግዚአብሔርን ፈሪ፣ ሰውን አክባሪ፣ ለሃገር ጠቃሚ አድርገን" የሁልጊዜ የእዳዬ እና የልጆቻቸው ጸሎት ነው።

የተጣሉ ልጆች፣ ከሞት አፋፍ እና ከተለያየ ሁኔታ የመጡ ልጆችን ሰብስበው 'በራሳቸው ሞዴል' አሳድገዋል።

አዳዬ ልጆቻቸው በፍላጎታቸው መሠረት እንዲያድጉ ነበር ፍላጎታቸው።

አለም ደግሞ ፍላጎቷ ወደ ሩጫ እያደላ መጣ። ይኼንኑ ለማሳካትም ላይ ታች ማለት ጀመረች።

አንድም በሩጫ ለመሳተፍ የመረጠችው "እናት እና አባቴን ማስተዋወቅ አለብኝ" ከሚል ጽኑ ሃሳብ ነው።

ከዚያ በኋላ ሁሉም ነገር ሩጫ ሆነ።

"ስላላክ ሩጫ ነው። ከትምህርት ቤት ወጥቼ ወደ ቤት ስመለስ ከተቀደምኩን በረከቴ የተወሰደብኝ ይመስለኝ ነበር" ትላለች።

እዳዬ የልጆቻቸውን ፍላጎት ለማሳካት የማይቆፍሩት ጉድጓድ የለም።

የአለምን ፍላጎት በማየት የሩጫ አሰልጣኝ ቀጠሩላት። "'ልጄን አደራ' ብለው ደሞዝ እየከፈሉ እንደሰለጥን አደረጉ" ስትል ታስታውሳለች።

"በአጭር ጊዜ ውጤታማ ሆንኩኝ" ትበል እንጂ ውጤታማነት ለእሷ "ህልምን እና ራዕይን ማስቀጠል ነው። መድረስ ያለብን ደረጃ መድረስ ነው።"

በዚህ መልኩ በግብርና፣ በአስተዳደርም ሆነ በሌላ ዘርፍ ተሰማርቶ ውጤታማ መሆን የእዳዬም ሆነ የልጆቻቸው ስኬት ነው።

ቅድሚያ የሚሰጠው "የሃገር ፍቅር እና ለሰው መኖር ነው።"

አለም ውጤታማ የምትባል ማራቶን አትሌት ነች። ከታዋቂ አትሌቶች ጋር ተወዳድራ ትልልቅ ድሎችንም በተለያዩ የዓለም ሃገራት አስመዝግባለች።

በርሊን፣ ሲንጋፖር፣ ኒው ዮርክ፣ ሐምቡርግ እና ዎልፍስ በርግ ውድድር ያደረገችባቸው እና በአንዳንዶቹም ድል ያስመዘገበችባቸው መድረኮች ናቸው።

ከደረሰባት የእግር ጉዳት በኋላ ወደ ቀድሞ ብቃቷ ባትመለስም አሁንም ከስፖርቱ አልተለየችም።

በአባት እና እናቷ መስመር መጓዝ የምትፈልገው አለም የኢትዮጵያን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ "የአቅም ውስንነት ያለባቸውን አትሌቶች ሰብስቤ መሥራት እፈልጋለሁ" ትላለች።

የካርልን ስም ለማስጠራት በእሳቸው ስም ውድድር ለማካሄድ እና አትሌቶችን ለማፍራት በመንቀሳቀስ ላይ ትገኛለች።

ኢትዮ-ካርል አትሌቲክስ ክለብ የሚል ድርጅት አቋቁማለች። በኮሮና ምክንያት በሚፈለገው ደረጃ ባይንቀሳቀሰም።

ሥራው ደግሞ ቀጣይ ሲሆን አትሌቶች በማፍራት የተሻለ ደረጃ ላይ ሲደርሱ የመጡበትን አካባቢ አንዲረዱ የሚያበረታታ ነው።

ቀጣይ ደግሞ በአበበች ጎበና ስም መሥራት ነው። "እሳቸው ኖሩ የሚባለው መቼ ነው ታድያ?" ትጠይቃለች። "ይህን ካልሠራንማ ሞተዋል ነው የሚባለው። ከመቶ ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያን ቀበርናቸው ማለት ነው።"

"አደራም አለብኝ። 'ልጄ አደራ ብዬሻለሁ እንዳትለይኝ' ብለውኛል።"

እዳዬ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ 70 በላይ ሽልማት ማግኘታቸውን የምትናገረው አለም " የሚሸለሙት ከዓለም ነው የሚሠሩት ግን ለኢትዮጵያ ነው" ትላለች።

ለዚህ ደግሞ መንግሥት እና ህዝቡ በጋራ ሊተባበር እንደሚገባ ትናገራለች።

አሁንም ልጆቻቸው ስላሉ "ቋሚ ገቢ የሚገኝበት እና በየክልሉ ካርል እና አበበች ጎበና የሚሠሩት ሥራ መስፋፋት አለበት" ብላለች።

ሁሉም ልጆቻቸው ከማዕከሉ ከወጡ በኋላ በዓልን ጨምሮ በየጊዜው ይጠይቋቸዋል። ልጆች እናቶቻቸውን እንደሚጠይቁት።

የኮሮና ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ እዳዬን ማገኘት ተከልክሎ ነበር። ያለፈው አንድ ዓመት ከምናምን ለልጆቻቸው እናታቸውን ማየት ባለመቻላቸው አስቸጋሪ ነበር። ልጆቻቸው ግን ቢያንስ ወደ ማዕከሉ አካባቢ በማቅናት ተሰባስበው ሲያስቧቸው ቆይተዋል።

"አሁን ያለሁበት ዓለም ሌላ ነው። የበፊቱ ደግሞ ሌላ ነው " የምትለው አትሌት አለም "የአበበች ጎበና ድርጅት [እርሳቸው ካገኙት በእጥፍ አድጎ] 140 ሽልማቶችን እንዲያገኝ መሥራት አለብን" ትላለች።