ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካና የኔቶ ጦሮች ከአፍጋኒስታን ጠቅልለው ወጡ
የአሜሪካና የየሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን አገሮች ድርጅት (ኔቶ) የጦር ኃይሎች ከአፍጋኒስታን ጠቅልለው ወጥተዋል።
ለ20 አመታት ያህል ታጣቂዎችን እንዋጋለን ብለው የገቡት እነዚህ የጦር ኃይሎች በመጨረሻም በባግራም የጦር ሰፈር የነበራቸውን ኃይል አውጥተዋል።
የነዚህ ጦር ኃይሎች አፍጋኒስታንን ለቆ መውጣት የውጭ አገር ኃይሎች በሙሉ ጠቅልለው መውጣታቸውን አመላካች ነው ተብሏል።
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የአሜሪካ የጦር ኃይል መስከረም 1 ሙሉ በሙሉ ጠቅልለው ይወጣሉ ብለው ነበር።
በተመሳሳይ ዋነኛው የጂሃዲስት ቡድን ታሊባን በአፍጋኒስታን ግዛቶችን ለመቆጣጠር እየገሰገም መሆኑ ተገልጿል።
አሜሪካ ጠቅልዬ እወጣበታለሁ ያለችው መስከረም 1 ወይም በአውሮፓውያኑ 11 በአሜሪካ ላይ በ2001 የደረሰው ጥቃት መታሰቢያ ዕለት ነው።
በዚህ ጥቃት 3 ሺህ ያህል ሰዎች ተገድለዋል።
ጥቃቱ የተፈፀመው በወቅቱ በአፍጋኒስታን ተቀማጭነቱን ያደረገው በአለም አቀፉ የጂሃዲስት ቡድን አልቃይዳ ነው።
አልቃይዳ በአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ ጀምሮ ስልጣን ላይ የነበረው ታሊባንም ታግዟል ተብሏል።
ከአመት በኋላም በአሜሪካ የሚመራው ጥምር ኃይልም አፍጋኒስታንን በመውረር ሁለቱንም ኃይሎች አሸንፏል።
አሜሪካ ለረዥም አመታት ያደረገችውን እንዲሁም በሰው ልጅ ህይወትም ሆነ ከፍተኛ ገንዘብ ያስወጣትን ጦርነት መቋጨት ትፈልጋለች።
የፀጥታውንም ሁኔታ ለአፍጋኒስታን መንግሥት ለቅቃ አሜሪካ ወጥታለች።
ነገር ግን ከ2 ሺህ 500 እስከ 3 ሺህ 500 የሚሆኑ ወታደሮቿ በአፍጋኒስታን ይቆያሉ ተብሎ ታስቦ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት መውጣታቸውን ተከትሎ ከአንድ ሺህ የሚያንሱ ወታደሮች ብቻ ቀርተዋል።
ከግንቦት ወር ወዲህ 7 ሺህ የሚሆኑ የጥምር ኃይሉ ወታደሮች በአፍጋኒስታን የነበሩ ሲሆን አብዛኛዎቹም ለቀው እንደወጡ ይታመናል።
ጀርመንና ጣልያን በያዝነው ረቡዕ ዘመቻቸውን ማጠናቃቸውንም አስታውቀዋል።
በአሁኑ ወቅት ታሊባን በርካታ ግዛቶችን እየተቆጣጠረ ሲሆን በአገሪቱም ላይ የርስ በርስ ጦርነት እንዳይፈጠር ተሰግቷል።