የአውስትራሊያ ዩኒቨርስቲዎች በቻይና ጉዳይ ጫና ሥር ወድቀዋል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአውስትራሊያ የሚማሩ ቻይናዊያን የዲሞክራሲ ደጋፊ ተማሪዎች በቻይና መንግሥት ዘንድ ቁጣን ሊቀሰቀሱ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ አስተያየት ከሰጡ ወከባ እና ቅጣት ይደርስብናል ብለው እንደሚፈሩ አንድ አዲስ ሪፖርት አስታወቀ።
ሂውማን ራይትስ ዎች በአውስትራሊያ ያሉት ተማሪዎች እንደሚሰለሉ ያምናሉ፤ በዚህም ብዙዎች በክፍል ውስጥ ራሳቸውን ሳንሱር ያደርጋሉ ብሏል።
ቻይናን የተመለከቱ ትምህርቶችን የሚያስተምሩ መምህራንም ራሳቸውን ሳንሱር ለማድረግ ጫናዎች እንዳሉባቸው ተናግረዋል።
የመብት ተሟጋች ቡድኑ እንዳመለከተው የተጠቀሱት ጫናዎች የአውስትራሊያ ዩኒቨርስቲዎችን የትምህርት ነጻነት ችላ ያለ ነው።
በአውስትራሊያ የከፍተኛ ትምህርት ሥርዓት ውስጥ ከፍለው የሚማሩ ቻይናውያን ተማሪዎች ጥገኛ ሲሆን ከኮሮናቫይረስ መከሰት በፊት በአገሪቱ ውስጥ ካሉ ዓለም አቀፍ ተማሪዎች ውስጥ 40 በመቶ ያህሉ ቻይናውያን ነበሩ።
በአሁኑ ጊዜ በአውስትራሊያ ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ 160,000 የሚጠጉ ቻይናውያን ተማሪዎች ይገኛሉ። በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት እየተበላሸ መምጣቱን ተከትሎ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ቻይና በአውስትራሊያ ያሉ ዩኒቨርሲተዎች ላይ የምታሳድረው ተጽዕኖ እየጨመረ መጥቷል።
ሂውማን ራይትስ ዎች 50 የሚጠጉ በአውስትራሊያ ያሉ ተማሪዎችን እና ምሁራንን ቃለ መጠይቅ ማድረጉን እና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተባባሰ የመጣ ‹‹የፍርሃት ድባብ›› መመልከቱን ገልጿል።
አጥኚዎቹ በአውስትራሊያ ያሉ ሦስት ተማሪዎች የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ተከትሎ ፖሊስ በቻይና የሚገኙ ቤተሰቦቻቸውን እንዳነጋገረ ጠቅሰዋል።
አንድ ተማሪም በአውስትራሊያ የትዊተር አካውንት በመክፈት ዴሞክራሲን የሚደግፉ መልዕክቶችን መለጠፉ ከቻይና ባለሥልጣናት የእስር ማስፈራሪያ እንደሚደርሰው ተገልጿል።
ብዙዎች የትምህርት ቤት ጓደኞቻቸው ለቻይና ኤምባሲ ሪፖርት እንደሚያደርጉ ፍራቻ እንዳላቸው ተናግረዋል።
‹‹በአውስትራሊያ ውስጥ ያደረጉት እንቅስቃሴ የቻይና ባለሥልጣናት አገር ቤት ያሉ ዘመዶቻቸውን ለመቅጣት ወይም ለመመርመር ሊዳርግ ይችላል የሚል ፍርሃት በእያንዳንዱ ቃለ መጠይቅ በተደረገለት የዴሞክራሲ ደጋፊ ተማሪ አዕምሮ ላይ ከባድ ጫና አሳድሯል›› ብሏል ሪፖርቱ።
ቃለ-መጠይቅ ከተደረገላቸው ተማሪዎች ውስጥ 11 ዱ ከዋናው ቻይና የመጡ ሲሆኑ 13ቱ ከሆንግ ኮንግ የመጡ ናቸው።
በአውስትራሊያ እ.ኤ.አ. በ2019 የሆንግ ኮንግ ተቃውሞ በኋላ ትንኮሳዎች መጨመራቸውን ተናግረዋል።
ሪፖርቱ ተማሪዎቹ ሰልፈኞቹን ከተቀላቀሉ በኋላ ወይም የቻይና መንግሥት ላይ ትችትን ከገለጹ በኋላ ተማሪዎች የቃላት ብሎም በበይነ መረብ ጥቃቶችን እንዳስተናገዱ አመልክቷል።
የግል መረጃዎቻቸው በበይነ መረብ ላይ እንደሚሰራጩ እና ተማሪዎቹም አብዛኛውን ጊዜ ያጋጠማቸውን ችግር ለዩኒቨርሲቲያቸው ሪፖርት አላደረጉም ብሏል-ሪፖርቱ።
‹‹ዩኒቨርሲቲያቸው ለብሔራዊ ስሜት ለሚከራከሩ ቻይናውያን ተማሪዎች ርህራሄ እንዳለው በማመን ወይም ከቻይና መንግሥት ጋር ያለውን ግንኙነት ለማስቀጠል ቅድሚያ እንደሚሰጥ በማመን እና ስጋታቸውን በቁም ነገር እንደማይመለከተው በማሰብ አያመለክቱም›› ሲል ሪፖርቱ ጠቅሷል።
የሪፖርቱ አዘጋጅ ሶፊ ማኪኔይል ‹‹ዩኒቨርሲቲዎቹ አስተዳዳሪዎች ከቻይና የመጡ ተማሪዎችን መብቶች የማስከበር እና የመንከባከብ ግዴታቸውን ሳይወጡ ቀርተዋል›› ብለዋል ።
አስጠኚዎች እና አስተማሪዎችም የሚደርስባቸው ጫና እየጨመረ መምጣቱን ሪፖርቱ ጠቅሷል።












