ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ፕሬዚዳንት የ15 ወራት እስር ተፈረደባቸው
የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ በመተላለፍ የ15 ወራት እስር ተፈረደባቸው።
ትዕዛዙን ያስተላለፈው የአገሪቱ ከፍተኛው የህገ መንግሥት ፍርድ ቤት ሲሆን የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ጥሰዋል በሚልም ነው ቅጣቱ የተጣለባቸው።
የቀድሞው ፕሬዚዳንት በስልጣን በነበሩበት ወቅት የእውነት አፈላላጊ ኮሚሽን በሙስና ያቀረበባቸውን ውንጀላ ፍርድ ቤት ቀርበው እንዲያስረዱ ቢጠየቁም ችሎት ባለመገኘት ትዕዛዝ መጣሳቸው ተመልክቷል።
ከሶስት አመት በፊት ከስልጣናቸው የተነሱት ዙማ የሙስና ክስ ቀርቦባቸዋል።
ዙማ ከቀረበቡባቸው ክሶች መካከል ብልጹግ የሚባሉትን ቢሊየነሮቹን የጉብታ ቤተሰብ አባላት የደቡብ አፍሪካን ሀብት እንዲቀራመቱ አድርገዋል የሚሉ ይገኙበታል።
የጉብታ ቤተሰብ በደቡብ አፍሪካ ፖሊሲ እንዲቀየር፣ የካቢኔ አባላት ሹም ሽር እስከማድረግ ተጽእኖ ነበራቸው፤ ይህም የሆነው በዙማ ምክንያት ነው ተብሏል።
ጃኮብ ዙማ በህገ መንግሥቱ ፍርድ ቤት በአንድ ችሎት ቢገኙም ከዚያ በኋላ ግን የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ በመተላለፍ በእምቢተኝነታቸው መቀጠላቸው ተገልጿል።
ኮሚሽኑን በበላይነት የሚመሩት ዳኛ ሬይመንድ ዞንዶ ህገ መንግሥታዊው ፍርድ ቤት ጣልቃ እንዲገባ ጠይቀዋል።
ፍርድ ቤቱ ይህንን ውሳኔ ቢያስተላልፍም የዙማ መታሰር ግልፅ አይደለም።
በተያያዘ ዜና በባለፈው ወር ዙማ በሙስና ክስ በቀረበባቸው ወንጀል ጥፋተኛ አይደለሁም ብለዋል።
ይህ ክስ በ1990ዎቹ የተደረገ የ5 ቢሊዮን ዶላር መሳሪያ ሽያጭ ጋር የተገናኘ እንደሆነም ተጠቅሷል።