ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኤስዋቲኒ የዴሞክራሲ ደጋፊዎች ሰልፈኞች ከፖሊስ ጋር ተጋጩ
ቀድሞ ስዋዚላንድ በመባል በምትታወቀው ኤስዋቲኒ የጸጥታ ኃይሎች የሕገ-መንግስታዊ ማሻሻያዎችን ከሚጠይቁ ሰልፈኞች ጋር ተጋጭተዋል፡፡
መንግሥት ሁሉም ሰልፎች ላይ ክልከላ ቢጥልም በዋነኛነት ወጣቶች የተሳተፉበት የተቃውሞ ሰልፎች ከሳምንቱ መጨረሻ ጀምሮ ተጠናክረዋል፡፡
ሰልፈኞቹ ነጻ ምርጫን ጨምሮ የዴሞክራሲያዊ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ ለንጉስ ምስዋቲ ጥሪ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡
ተቃውሞው እየተጠናከረ መምጣቱ ተከትሎ ንጉስ ምስዋቲ ከሃገር ተሰደው ሊሆን እንደሚችል ያልተረጋገጡ ዘገባዎች እየወጡ ነበር፡
የደቡብ አፍሪካ የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ኤስኤቢሲ ስለ ክሱ ዘገባ ሠርቷል፡፡
ተቀቃውሞ መጋጋሉን ተከትሎ ግጭቶች በከሰታቸው ነው ንጉሱ ሃገር ጥለው የተሰደዱት ተብሏል።
በግል የሚተዳደረው ስዋዚላንድ ኒውስ ድረ-ገጽ "ተቃውሞ ተባብሶ ግጭቶች በመፈጠራቸው ንጉስ ምስዋቲ ተሰደዋል" ሲል በትዊተር ገጹ አስፍሯል።
ዘውዳዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩረው ሮያል ሴንትራልም ዝረዝር መረጃ ሳይገልጽ "ሃገረ ጥለው ተሰደዋል" ሲል ዘግቧል።
በመላ ሃገሪቱ ቢያንስ በ10 የተለያዩ አካባቢዎች የተካሄዱትን የተቃውሞ ሰልፎችን ባለሥልጣኖች አግደዋል፡፡
የተቃውሞ ሰልፉ ወደ አመፅ ከተቀየረ በኋላ የጸጥታ ኃይሎች አንድን ሠላማዊ ሰው በጥይት መምታታቸውን ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡
የጸረ-ንጉሳዊ አገዛዙን የተቃውሞ እንቅስቃሴ የሚዘግብ ጋዜጠኛም ጉዳት ደርሶበታል፡፡
ንጉስ ምስዋቲ ሳልሳዊ አባታቸው ንጉስ ሶቡሁዛ ዳግማዊ ከሞቱ ከአራት ዓመታት በኋላ የዓለም በዕድሜ ትንሹ ንጉስ ሆነው እአአ በ 1986 ዙፋኑን ተረከቡ፡፡
ኤስዋቲኒ በአፍሪካ በፍፁም ንጉሳዊ አገዛዝ ሥር የምትገኝ የመጨረሻው ሀገር ናት፡፡