በአሜሪካና በካናዳ አደገኛ ሙቀት በመከሰቱ ባለሥልጣናት ነዋሪዎችን አስጠነቀቁ

ታትሟል

አስካሁን ከተመዘገበው ከፍተኛ የሙቀት መጠን ውስጥ የሚመደብ አደገኛ ነው የተባለ ከባድ ሙቀት በአሜሪካና በካናዳ ውስጥ መከሰቱ ተነገረ።

ይህንንም ተከትሎ የአሜሪካ ብሔራዊ የአየር ሁኔታ አገልግሎት በበርካታ የአገሪቱ አካባቢዎች ውስጥ ከመጠን ያለፈ ሙቀት ሊከሰት እንደሚችል አስጠንቅቋል።

ኦሪገን ግዛት ውስጥ የምትገኝ ከተማ ደግሞ ያለው የሙቀት መጠን "ለህይወት አደገኛ" ሊሆን እንሚችል ነዋሪዎቿን አስጠንቅቃለች።

አንዳንድ ከተሞችም የሙቀቱን ወላፈን ለማቀዝቀዝ የሚረዱ የማቀዝቀዣ መሳሪያዎች የተገጠሙላቸው ህንጻዎች ውስጥ ቀዝቃዛ ማዕከላትን በመክፈት ነዋሪዎቻቸው ከዚህ የከፋ ሙቀት እንዲጠለሉ እያደረጉ ነው።

ባለሙያዎች እንደሚሉት የአየር ሁኔታ ለውጥ በዓለም ላይ የሚያጋጥመውን እንዲህ አይነቱን እጅግ ከፍተኛ የሙቀት መጠን መከሰት ተደጋጋሚ ሊያደርገው ይችላል።

በአየር ሁኔታ ለውጡ የተነሳ በጎርፍ፣ በከባድ አውሎ ነፋስ እና በከባድ ሙቀት በርካታ ሰዎች ለሞት ሊዳረጉ እንደሚችሉ ሲሉ ባለሙያዎች እያስጠነቀቁ ነው።

የአሜሪካ የአየር ሁኔታ አገልግሎት ተቋም እንዳስጠነቀቀው በበርካታ የአገሪቱ አካባቢዎች ለቀጣይ ተጨማሪ ቀናት "እጅግ አደገኛ የሆነ የሙቀት መጠን" ሊኖር እንደሚችል ገልጿል።

አሁን እየተከሰተ ባለው ከባድ ሙቀት ምክንያት ከዚህ በፊት ከተመዘገበው ከፍተኛው ሙቀት የበለጠ ሊመዘገብ እንደሚችል ተሰግቷል።

ባለፈው ቅዳሜ ሲያትል ውስጥ የተመዘገበው 101 ፋራናይት የሙቀት መጠን በዚያ አካባቢ ሰኔ ውስጥ አጋጥሞ የማያውቅ የሙቀት መጠን ተብሎ ተመዝግቧል።

"ነዋሪዎች ለረጅም ጊዜ ከቤት ውጪ እንዳይቆዩ፣ በርከት ያለ ፈሳሽ እንዲወስዱና ቤተሰቦቻቸውና ጎረቤቶቻቸው ያሉበትን ሁኔታ በተደጋጋሚ እንዲከታተሉ ይመከራሉ" ብሏል የአሜሪካ የአየር ሁኔታ ተቋም።

ከዚህ ቀደም የተመጣጠነ ሙቀት የነበራቸው አካባቢዎች ውስጥ የሚገኙ ቤቶች የአየር ማቀዝቀዣ ያልበራቸው ሲሆን አሁን የተከሰተው ከባድ ሙቀት ግን እንዲቀዙ አስገድዷቸዋል።

ቀላል የአየር ማቀዝቀዣዎችን የሚሸጡ መደብሮች ሁሉንም ሸጠው የጨረሱ ሲሆን በሙቀቱ የተነሳ በርካታ የኮሮናቫይረስ ክትባት አገልግሎቶች እንዲቋረጡ ተደርገዋል።

ባለሥልጣናት ነዋሪዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ቢመክሩም በርካታ ሰዎች ፀሐዩን በመሞቅ ከቤት ውጪ ለማሳለፋቸው በሐይቅ ዳርቻዎችና በመዋኛ ገንዳዎች አካባቢ በብዛት እየተሰበሰቡ ነው።

የካናዳዋ ብሪቲሽ ኮሎምቢያ ባለፈው ቅዳሜ ከፍተኛ ተባለውን ሙቀት አስመዝግባለች። ከዚህ በተጨማሪ በበርካታ ግዛቶቿ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ሙቀት ተከስቷል።