ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በምዕራብ ኦሮሚያ አፍጋኒስታናውያን ታገቱ መባሉን የአካባቢው ባለሥልጣን አስተባበሉ
በምዕራብ ወለጋ መነሲቡ ወረዳ በማዕድን ማውጣት ሥራ ላይ የተሰማሩ ሁለት የውጭ አገር ዜጎች በታጣቂ ቡድን ታግተዋል የተባለው ሐሰት መሆኑን አንድ የአካባቢው ባለሥልጣን አስተባበሉ።
በምዕራብ እና ደቡብ ኦሮሚያ እንደሚቀሳቀስ የሚነገረው የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች ሁለት ለማዕድን አውጪ ድርጅት ይሰራሉ ያሏቸውን የአፍጋኒስታን ዜጎችን በመነሲቡ ወረዳ ማገታቸውን መግለጻቸውን ተከትሎ ነው ባለስልጣኑ ምላሽ ሰጡት።
በአካባቢው ተፈጸመ ስለተባለው እገታ በቢቢሲ የተጠየቁት የምዕራብ ወለጋ ዞን ኃላፊ አቶ ኤሊያስ ኡመታ ድርጊቱ አልተከሰትም በማለት አስተባብለዋል።
ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራውና መንግሥት 'ሸኔ' በሚል የሚጠራው ይህ ቡድን አገትኳቸው ያላቸው ግለሰቦች በአካባቢው ማዕድን ለሚያወጣ ድርጅት የሚሰሩ እንደሆኑ ባወጣው መግለጫ ላይ ተናግሯል።
ቢቢሲ ስለግለሰቦቹ መታገትም ሆነ ይህ ድርጊት ተፈፀመ የተባለበት ስፍራ መነሲቡ መሆኑን ከገለልተኛ ወገን አላረጋገጠም።
የምዕራብ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ኤሊያስ ኡመታ "አፍጋኒስታናዊ እኛ ጋር የለም፤ ዞናችንን በደንብ ነው የምናውቀው" በማለት ድርጊቱ ስለመፈፀሙ እንደማያውቁ ተናግረዋል።
በልዩ ልዩ ግድያዎች እና ጥቃቶች በመንግሥት እና በሕዝቡ የሚከሰሰው ይህ ቡድን ከአንድ ወር በፊት በኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት ተፈርጇል።
ቡድኑ በተለያዩ ጊዜ ከተፈጸሙ ጥቃቶች ጋር በተያያዘ ተደጋጋሚ ክሶች ሲቀርቡበት የቆ ሲሆን ክሶቹን በዝምታ ሲያልፋቸው አንዳንዶቹንም ሲያስተባብል ቆይቷል።
አሁን ፈጸምኩት ያለው እገታ ሁለተኛው ሲሆን ከዚህ ቀደም ሲል ሦስት በማዕድን ማውጣት ሥራ ላይ ተሰማርተው ነበር ያላቸውን የቻይና ዜጎችን ካገተ በኋላ ለዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር አሳልፎ መስጠቱ መገለጹ ይታወሳል።
በወቅቱ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት እንዲሁም የዞኑም ሆነ የመነሲቡ ወረዳ ባለሥልጣናት ይህ ድርጊት በአካባቢው ስለመፈፀሙ አስተባበለው ነበር።
የመነሲቡ ወረዳን የሚያዋስነው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የፖሊስ ኃላፊም ለቢቢሲ ተመሳሳይ ምላሽ ሰጥተው ነበር።
ከቀናት በኋላ ግን የዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር (አይሲአርሲ) ሦስቱን የቻይና ዜጎች አዲስ አበባ ለሚገኘው የቻይና ኤምባሲ እንዲሰጡ ማመቻቸቱን በወቅቱ ለቢቢሲ አረጋግጧል።
'መረጃ የለኝም'
ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር ፓርቲ ተገንጥሎ የሚንቀሳቀሰው ይህ ቡድን 'ሙን ሮክ ማይኒንግ ኤንድ ማርብል ዴቬሎፕመንት' ለሚባለው ኩባንያ የሚሰሩ ናቸው ያላቸውን ሁለት የአፍጋኒስታን ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች ማገቱን ይናገራል።
ቡድኑ ድርጊቱ የተፈፀመበት ቦታ በምዕራብ ወለጋ ዞን መነሲቡ ወረዳ መሆኑንም ጨምሮ አስታውቋል።
በመግለጫውም ላይ የታገቱት ግለሰቦች ስም የተገለፀ ሲሆን ምስላቸውም ተያይዞ ቀርቧል።
በትዊተር ላይ በወጣው መግለጫ እና የግንባሩ የዓለም አቀፍ ቃል አቀባይ ናቸው በተባሉት ኦዳ ተርቢ ስም በተከፈተ ገጽ ላይ የታገቱትን ግለሰቦቹን የደኅንነት ሁኔታን በሚመለከት "በጥሩ ሁኔታ ላይ ናቸው" የሚል መረጃ ሰፍሯል።
ነገር ግን በመግለጫው ላይ እነዚህ ታግተዋል የተባሉት ሰዎች ሚና ምን እንደሆነ አልተገለፀም።
ቢቢሲ ማዕድን አውጪ ኩባንያ ነው የተባለውን ድርጅት ማንነት በሚመለከት ሙሉ መረጃ ለማግኘትና ታገቱ ስለተባሉት ግለሰቦች ለማጣራት ጥረት ቢያደርግም አልተሳካለትም።
ስለ እገታው የተጠየቁት የምዕራብ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ኤልያስ ኡመታ "መረጃ የለኝም" በማለት ተናግረዋል።
"መረጃው የለንም፤ እንደዚህ ዓይነት ወሬ አንከታተልም። እንዲህ የሚባል ነገር የለም። በየሰዓቱ ሪፖርት ይደርሰናል። ማንም ሰው የሚለጥፈውን አንስታችሁ ራሳችሁም አትጨነቁበት እኛንም አታጨናንቁን" በማለት ለጠየቅናቸው ጥያቄ በቁጣ መልሰዋል።
"አፍጋኒስታናዊ እኛ ጋር የለም፤ ዞናችንን በደንብ እናውቃለን፤ የውጪ አገር ዜጋ የት የት እንዳለ በደንብ እናውቃለን። ሪፖርት ደግሞ ከቀበሌ ወደ ወረዳ፣ ከወረዳ ወደ ዞን 24 ሰዓት ሙሉ የምንከታተልበት ሰንሰለት ስላለን እንዲህ ዓይነት መረጃ የለኝም" በማለት የተባለው እገታ አለመከሰቱን ገልጸዋል።
ይህ ቡድን ከዚህ በፊትም የቻይና ዜጎችን ባገተበት ወቅት በአካባቢው ማዕድን በማውጣት ሥራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች የአካባቢውን የተፈጥሮ ሀብት እያወደሙ ነው በማለት ወንጅሏቸው ነበር።
በተጨማሪም እነዚህ ሰዎች ከመንግሥት ጋር ያላቸው ስምምነትን እንደማይቀበለውም ገልጾ ነበር።
ታጣቂው ቡድን በዚህ ዓመት ብቻ በጉሊሶ ወረዳ፣ ባቦ ገምቤል አቤ ደንጎሮ እና በሌሎች ወረዳዎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ ለተፈፀሙ ግድያዎች በመንግሥት እና በነዋሪዎች ይከሰሳል።
ይሁን እንጂ እነዚህ ታጣቂዎች በንፁሃን ዜጎቸ ላይ ጥቃት አናደርስም በማለት በተደጋጋሚ ያስተባብላሉ።
በአካባቢው ከዚህ በፊትም የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችና ፕሬዝዳንቱን ዶ/ር ደለሳ ቡልቻ፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት አባገዳዎች እና የባንክ ሠራተኞች ጨምሮ ታግተው ያውቃሉ።