ስዊዘርላንድ ፀረ-ተባዮችን ለማገድ ህዝበ ውሳኔ ልታካሂድ ነው

በስዊዘርላንድ በሬዎች ሳር እየጋጡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ስዊዘርላንዳውያን ሰሞኑን አገራቸው ኬሚካል ያላቸውን ፀረ-ተባዮች ለማገድ በምታደርገው ህዝበ ውሳኔ ላይ ድምፅ ስጡ ተብለዋል።

ይህ ህዝበ ውሳኔ ከፍተኛ ድምፅ ማግኘት ከቻለ ሰዊዘርላንድ ፀረ-ተባዮችን በማገድ ከአለም ሁለተኛዋ ትሆናለች።

መንግሥት ፀረ-ተባዮችን የሚጠቀሙ አርሶ አደሮችንም እንዳይጠቀሙ ለማድረግ ድጋፍ የሚያደርገውን ድጋፍ አቆማለሁ የሚል ሃሳብን ያስቀረበ ሲሆን በሌላኛው ሃሳብ ደግሞ በአስር አመት ውስጥ ሁሉንም ማገድ የሚል ነው።

ፀረ-ተባዮች ይታገዱ የሚሉ አካላት በአገሪቱ ውስጥ ባሉ ውሃ አካላት፣ አዝርዕት፣ እፅዋትና እንስሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳቶች እያደረሱ ነው ይላሉ።

"ፀረ-ተባዮች ይታገዱ በሚል ድምፄን እሰጣለሁ። ስለወደፊቱ ማሰብ አለብን። ፀረ-ተባዮች ጤናችንን ይጎዳሉ" በማለት የጄኔቫ ነዋሪ የሆኑት ማሪ ሌናቡስ ተናግረዋል።

ፀረ-ተባዮችን ይታገዱ በማለት ከፍተኛ ንቅናቄ እያደረጉ የሚገኙት የከተማ ወጣት ዽምፅ ሰጭዎች ናቸው።

የስዊዘርላንድ አርሶ አደሮች በበኩላቸው ይህ እግድ የኑሮ ሁኔታቸውን እንደሚጎዳው እየተናገሩም ነው፤ ከስራ ውጭም ያደርገናል በሚል ፍራቻቸውን እየገለፁ ነው።

የፀረ-ተባዮች እግድ በከፍተኛ ድምፅ ማግኘት ከቻለ አገሪቱ ፀረ-ተባዮችን ካገዱ ጥቂት ከተሞችና ግዛቶች ውስጥ አንዷ ትሆናለች።

ከዚህም በተጨማሪ የስዊዘርላንድ ፀረ-ተባዮችን ማገድ ከፍተኛ የሆነ አለምአቀፋዊ ለውጥም ያመጣል ተብሏል።

ለዚህም እንደ ምክንያትነት የተሰጠው ስዊዘርላንድ ፀረ-ተባዮችን በማምረት በአለም ዘንድ ቀዳሚ በመሆንዋ ነው።

በዛሬው ዕለት ከፀረ-ተባዮች እግድ በተጨማሪ በስዊዘርላንድ በፀረ-ሽብር ረቂቅ ህግ፣ በኮቪድ-19 አስቸኳይ ፈንድ ላይም ድምፅ ይሰጣል።

ቀጥተኛ ዲሞክራሲ ከሚከተሉ አገራት አንዷ የሆነችው ስዊዘርላንድ ማንኛውም ውሳኔ ህዝቡ የሚሳተፍበት ሲሆን በድምፅ ብልጫም የሚበየን ይሆናል።

አገር አቀፍ ድምፅም እንዲያገኝ ለማድረግ ዘመቻ የሚያካሂዱት አካላት በመቶ ሺህ የሚቆጠር ፊርማ መሰብሰብ ይጠበቅባቸዋል።