ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በጣልያን የጠፋችው ወጣት በቤተሰቦቿ ሳትገደል እንዳልቀረች ፖሊስ አስታወቀ
በሰሜን ጣልያን ሳማን አባስ የተባች አንዲት የ18 አመት ወጣት መጥፋቷን ተከትሎ ቤተሰቦቿ በግድያ ወንጀል ተጠርጥረው ምርመራ ተከፍቶባቸዋል።
እንደፖሊስ ከሆነ ባለፈው ዓመት የሳማን አባስ ቤተሰቦች ወደ ፓኪስታን አቅንታ በግድ ሊያጋቧት ቢሞክሩም ፈቃደኛ ባለመሆኗ በዚያ በተነሳ ቁርሾ ቤተሰቦቿ ሳይገድሏት እንዳልቀሩ መረጃዎች አግኝቻለሁ ብሏል ፖሊስ።
የአጎቷ ልጅ ፈረንሳይ ውስጥ ተይዞ ለጣሊያን ተላልፎ ተሰጥቷል፡፡
ወላጆቿ ወደ ትውልድ ቦታቸው ፓኪስታን መጓዛቸው የተዘገበ ሲሆን ንክኪ አላቸው የተባሉ አጎቷና ሌላ የአጎት ልጅ ደብዛቸው ጠፍቷል።
እንደዓቃቤ ህግ ከሆነ አምስቱም በመግደል እና አስከሬን በመጣል የተጠረጠሩ ቢሆንም እስካሁን ምንም አይነት የወጣቷ አካል አልተገኘም፡፡
ከሳማን አባስ መጥፋት በኋላ ከጣሊያናዊ ጋዜጠኛ ጋር ቆይታ ያደረጉት አባቷ ቤልጅየም መሄዷን ተናግረዋል፡፡
የጣሊያን መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ከጥቅምት ወር ጀምሮ በማህበራዊ አገልግሎቶች ጥበቃ ሥር የኖረች ሲሆን መጋቢት መጨረሻ ላይ በፓርማ አቅራቢያ ኖቬላራራ ወደሚገኘው የቤተሰቧ ቤት ተመልሳለች፡፡
ዓቃቤ ህግ ኢዛቤላ ቺኤሲ እንዳሉት ቤተሰቦቿ አታለው ወደ ቤቷ እንድትመለስ ማድረጋቸውን ባለስልጣናቱ ያምናሉ ብለዋል፡፡ ሆን ተብሎ የታቀደ ግድያ መፈጸሙን ገልጸው በህይወት ትገኛለች የሚል ምንም ፍንጭ የለም ብለዋል።
ፖሊስ ከኖቬላራ አቅራቢያ የሚገኝ የእርሻ መሬትን ከግንቦት መጀመሪያ ጀምሮ በማሰስ ላይ ሲሆን አፈሩን ውስጥ በጥልቀት ለመፈለግ የኤሌክትሮ ማግኔቲክ መሣሪያዎችን መጠቀም ጀምሯል፡፡
ባለሥልጣናት ተገደለች ብለው ከሚያምኑበት ከመጋቢት 29 ቀን በፊት የተቀረጸ ነው ያሉትን ቪዲዮ ለቀዋል። ቪዲዮው ከተጠርጣሪዎቹ መካከል ሦስቱ አካፋ፣ የብረት መቆፈሪያ እና ሰማያዊ ሻንጣ ይዘው ሲሄዱ ያሳያል፡፡
በሌላ ቀረጻ ደግሞ በቀጣዩ ቀን የጠፋችው ወጣት ከወላጆቿ ጋር ከቤት ስትወጣ ያሳያል።
ባለፈው ሳምንት የጣልያን የሙስሊም ህብረት የሳማን አባስን መሰወር ተከትሎ የግዳጅ ጋብቻን ውድቅ በማድረግ ፈትዋ (ሃይማኖታዊ ብይን) አውጥቷል፡፡